የመጠጥ ውሃ ችግር እንዲፈታላቸው በሐረር ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ

180

ሐረር ፤ ሚያዝያ 6 ቀን 2014(ኢዜአ) ያጋጠማቸው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር እንዲፈተላቸው በሐረር ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ።

የሐረሪ ክልል የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በበኩሉ፤  በኤረር የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ላይ ያጋጠመው ችግር ለመፍታት በተደረገው ጥረት እየተስተካከለ መምጣቱን  ገልጿል።

ነዋሪዎቹ እንዳመለከቱት፤ በከተማዋ በቂ ውሃ ባለመኖሩ ለመጠጥና ለንጽህና አገልግሎት የሚያስፈልጋቸውን በማጣት ተቸግረዋል።

የከተማው ነዋሪ አብዲ አዱስ፤ በሐረር ውሃ ለማግኘት ረጅም ርቀት መጓዝ ግዴታ መሆኑን ገልጸው፤ መንግስት ለችግሩ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

''የውሃ ችግሩ ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተዳምሮ ለተጨማሪ ወጪ ዳርጎናል'' ያሉት ደግሞ በከተማው የ06 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አልማዝ ማሞ ናቸው።

ውሃ ፍለጋ ረጅም መንገድ እንደሚጓዙ አመልክተው፤ ሌላው በአማራጭነት  ጨዋማ የጉድጓድ ውሃ ለመጠቀም መገደዳቸውን ተናግረዋል።

ወይዘሮ  ያስሚን አብዲ በበኩላቸው፤ ውሃ በወቅቱ ባለመምጣቱ ምክንያት አስፈላጊውን ጽዳት ስራ ለመከወን መቸገራቸውን በመግለጽ መንግስት ችግሩን ለመፍታት እንዲሰራ ጠይቀዋል።

ስለጉዳዩ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሐረሪ ክልል ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የቴክኒክና ኦፕሬሽን ዋና የስራ ሂደት ባለቤት አቶ አዲል በክሪ፤ ባለፉት ሁለት ወራት በኤረር የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ላይ የፓምፕ መሰበርና መቃጠል ሳቢያ የውሃ አቅርቦት ችግር እንዳጋጠመ ገልጸዋል።

ከአሁን ቀደም በሁለት ፓምፖች ግፊት ለነዋሪዎች ይቀርብ የነበረው ውሃ በአንድ ፓምፕ ብቻ ውሃ  እየተገፋ ለነዋሪዎች ይቀርብ ስለነበር አቅርቦት እንዲቀንስ  ማድረጉን አስረድተዋል።

ሆኖም ወቅቱ  በጋ እንደመሆኑ የውሃው  መጠን ቢቀንስም፤ለነዋሪዎቹ በሚቀርበው የውሃ መጠን ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር  አይደለም ብለዋል።

የሐረር ከተማ  ውሃ የምታገኘው ከድሬዳዋ አስተዳደር አሰሊሶና በሐረሪ ክልል ኤረር ወረዳ ቂሌ ቀበሌዎች ከተቆፈሩ ጉድጓዶች መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም