በ2014/15 የምርት ዘመን 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም በማረስ ገበያ መር ሰብል ለማልማት ታቅዷል

244

ሚያዝያ 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) በ2014/15 የምርት ዘመን 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም በማረስ ገበያ መር ሰብል ለማልማት መታቀዱን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ገለጸ።

በዚሁ አሰራር ከ1 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግም ታስቧል።

በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተር ዳይሬክተር ተጫነ አዱኛ ግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ወይም ገበያ ተኮር የኩታ ገጠም እርሻ ግብርናውን የማሸጋገር የትኩረት አቅጣጫ ተደርጓል ይላሉ።

የኩታ ገጠም እርሻ የአርሶ አደሩን ዝቅተኛ አመራረት ከማሻሻል በተጨማሪ በገበያ በማስተሳሰርና የተሻለ ጥቅም በማስገኘት ተመራጭ የግብርና ዘዴ ያደርገዋል።

በተመረጡ ሰብሎችና አካባቢዎች ላይ ውጤት ተኮር ግብርና ገቢራዊ ተደርጎ ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በዚሁ የአስተራረስ ዘዴ ስንዴን በሄክታር ከ30 ወደ 45 ኩንታል፤ በቆሎን ደግሞ ከ40 ወደ 60 ኩንታል ማምረት መቻሉን ጠቅሰዋል።

ኢንስቲትዩቱ በአምስት ዓመቱ የኩታ ገጠም እርሻ ትግበራ ፕሮጀክትን በመተግበር 4 ሚሊየን አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ በዕቅድ እየሰራ እንደሆነ ገልጸው፤ ትግበራው ሁለት ዓመት ተኩል እንዳስቆጠረ ገልጸዋል።

የግብርና ኮሜርሻላይዜሸን ክላስተር ፕሮጀክት ገበያውን፣ የሚያስፈልገውን ግብዓትና የአርሶ አደሩን የማምረት አቅም በማጥናት ከተተገበረ በኋላም ምርቱን ከገበያው ጋር የማስተሳሰር ሥራ እንዳለ ገልጸዋል።

አርሶ አደሮችን በግብርናው እሴት ሰንሰለት ተጠቃሚ በማድረግ ከራሳቸው ፍጆታ ባለፈ ምርታቸውን ለገበያ እንዲያቀርቡና ዘላቂ የመተማመንና የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ ማድረግ ነው ብለዋል።

በባለፈው የምርት ዘመን በክላስተር 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት መልማቱን ያስታወሱት አቶ ተጫነ ዘንድሮ ወደ 2 ነጥብ 6 ሄክታር ለማሳደግ ታቅዷል ብለዋል።

ከሰብል፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ በድምሩ አሥር የዘር አይነቶችን በገበያ ተኮር በክላስተር ለማልማት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም