የሶዶ ግብርና ኮሌጅ የከተማ ግብርናን ለማስፋፋት በሰርቶ ማሳያ ነዋሪዎችን እየደገፈ ነው

166

ሚያዝያ 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሶዶ ግብርና ኮሌጅ ከመማር ማስተማር ሥራ በተጓዳኝ የከተማ ግብርናን ለማስፋፋት የሰርቶ ማሳያ አዘጋጅቶ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎችን እየደገፈ መሆኑን አስታወቀ።

የኮሌጁ ዲን ረዳት ፕሮፌሰር መርክነህ መሰኔ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከህዳር ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ 800 የከተማዋ ነዋሪዎች የግብርና ልማት ስልጠና ተሰጥቷቸው ወደ ስራ ገብተዋል።

ለሰልጣኞቹ ምርጥ ዘር፣ ችግኝ፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያና መሠል ግብዓቶችን በማቅረብ ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችል ድጋፍ እንደተደረገላቸው ጠቅሰዋል።

በቆሎ፣ ስንዴ፣ ቲማቲም፣ ቆስጣ፣ ጎመንና ሌሎች ሰብሎችን የሚያመርተው ኮሌጁ የከተማ ግብርና ስራ አጥነትን በማቃለል ህብረተሰቡ የኑሮ ውድነትን እንዲቋቋም የሚያግዝ ስራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ወደ ስራ የገቡ ዜጎች ያላቸውን ቁርጠኝነትና ውጤታማነት በመከታተል ለሌሎች አርዓያ እንዲሆኑ ለማስቻል  እንደሚሰራም አመልክተዋል።

ኮሌጁ ከተለያዩ አካባቢዎች ለመጡ 1 ሺህ ሰዎች የከተማ ግብርና ሥራ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በኮሌጁ የሰብል ልማት ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ መርክነህ መጃ በበኩላቸው የከተማ ግብርናን በማስፋፋት ህብረተሰቡ ጤናማ የአመጋገብ ስርዓትን እንዲከተል እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

የከተማ ግብርና ስራዎችን ለማከናወን ውስን ቦታዎችን በአግባቡ መጠቀም ወሳኝ እንደሆነም አመልክተዋል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ በከተማ ግብርና ልማት የተሰማሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ቀደም ብለው ስራውን ቢጀምሩ የተሻለ ጥቅም ያገኙ እንደነበር ጠቅሰዋል።

የጓሮ አትክልት በማልማት ኑሯቸውን መደጎም መጀመር መቻላቸውን ገልጸው፤ ወደፊት የከተማ ግብርና ስራዎችን ለመስራት ዝግጁ እንደሆኑ ተናግረዋል።

ከግብርና ኮሌጁ በተሰጣቸው ስልጠና መሠረት እየሰሩ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም