በመዲናዋ ድጎማ የሚያደርግባቸው መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶች ሥርጭት ለመቆጣጠር የሚያስችል ዘመናዊ የቁጥጥር ሥርዓት ሊዘረጋ ነው

419

ሚያዚያ 5/2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ድጎማ ተደርጎባቸው በሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራት የሚፋፈሉ መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶች ሥርጭት ለመቆጣጠር የሚያስችል ዘመናዊ የቁጥጥር ሥርዓት ሊዘረጋ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዳንኤል መኢሳ እንደገለጹት፤ በመዲናዋ 121 የሚደርሱ የሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራት ይገኛሉ።

እነዚህም የሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራት ድጎማ የሚደረግባቸውን መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶች ለኅብረተሰቡ እያከፋፈሉና የዋጋ ንረቱን ለማቃለል እየሰሩ ነው ብለዋል።   

ያም ሆኖ አንዳንድ የሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራት በሕገ-ወጥ መልኩ መሰረታዊ የፍጆታ እቅዎቹን ላልተገባ አካል ሲያከፋፍሉ ቢሮው እንደደረሰባቸው ነው የጠቆሙት።

ይህንንም ተከትሎ ቢሮው በእነዚህ ማኅበራት ሕጋዊ እርምጃ መወሰዱን ጠቅሰው በቀጣይም ተመሳሳይ ድርጊት በሚፈጽሙ ማኅበራት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ያጠናክራል ብለዋል።  

አንዳንድ የሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራት የሚፈጽሟቸውን ሕገ-ወጥ ተግባራት በዘላቂነት ለመከላከል ዘመናዊ የቁጥጥር ሥርዓት ለመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

እነዚህን የፍጆታ ምርቶች ከክምችት ጀምሮ እስከ ተጠቃሚው ድረስ እንዴት እንደሚደርሱና መቆጣጠር እንደሚቻል የሚያግዝ ሶፍትዌር ላለፉት ስድስት ወራት ሲዘጋጅ አብራርተዋል።

ከዚህ ቀደም የነበረውን የኩፖን ሥርዓት በአዲስ ቴክኖሎጂ የሚተካ መሆኑን ጠቁመው ኅብረተሰቡ ምርቶቹን በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉና መረጃ እንዲለዋወጡ ያግዛል ብለዋል።       

አሁን ላይም ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓት ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ በሁለት ክፍለ ከተሞች ላይ የሙከራ ሥራው እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሙከራው በሁለት ክፍለ ከተሞች የተጀመረ ሲሆን በዋናነት በመንግሥት የሚቀርቡ የድጎማ ምርቶችን ያለምንም ክፍያ ማኅበራቱ ቤት ለቤት እንዲያቀርቡ የታለ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንንም ለማሳለጥ ሸማቾች በእጃቸው የሚይዙት ዘመናዊ ካርድ መዘጋጀቱን በመጠቆም።   

በኮልፌ ቀራኒዮ ወረዳ 9 የአገልግሎት ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አዋሽ መሃመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ የንግዱን አሰራር ለማዘመን ያስችላል ብለዋል።

በተለይም ለአዛውንቶችና አቅመ ደካሞች እንዲሁም ለአካል ጉዳተኞችን ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢዜአ ቤት ለቤት የስኳር ኮታቸውን ሲረከቡ ያገኘናቸው ሽማቾችን መካከል ወይዘሮ ገናነሽ ተኸርቁ ሸማች ናአቶ ቡሴር  ኡስማን ሸማች መካከል  አዲሱ የኩፖን አሰራር ምቹ መሆኑን ነው የጠቆሙት።  

መሰረታዊ ፍጆታዎችን ቤት ለቤት መቅረባቸው ከእንግልት እንደተረፉና ጊዜያቸውን እንደቆጠበላቸው ተናግረዋል።

ዘመናዊ የቁጥጥር ሥርዓት በቅርቡ በከተማ ደረጃ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን እስከ 3 ሺህ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ እድል ይፈጥራል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም