በክልሉ ፍርድ ቤቶች የተገልጋዮች እርካታ 65 በመቶ እንደሆነ በጥናት ተረጋገጠ

411

ባህር ዳር ሚያዚያ 5/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በየደረጃው በሚገኙ ፍርድ ቤቶች በተደረገ ጥናት የተገልጋዮች እርካታ 65 በመቶ እንደሆነ ማረጋገጥ መቻሉን የጥናቱ ቡድን አስተባባሪ አስታወቁ ።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት ያስጠናውና የፍርድ ቤቶችን የደንበኞች እርካታ ደረጃ የሚያሳይ የጥናት ውጤት በባህር ዳር ከተማ ውይይት ተደርጎበታል።

የጥናት ቡድኑ አስተባባሪና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት መምህር አቶ በለጠ አዲስ እንደገለጹት፣ ሳይንሳዊ ጥናቱ በየደረጃው ያሉ ፍርድ ቤቶች እየሰጡት ባለው አገልግሎት የደንበኞች እርካታ  የሚያሳይ ነው።

ጥናቱ የተካሄደው በአራት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምድብ ችሎቶች፣ በ11 ከፍተኛ ፍርድ ቤቶችና በ30 የተመረጡ የወረዳ ፍርድ ቤቶች መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚሁ ጥናት ሰባት ተመራማሪዎች፣ 77 መረጃ ሰብሳቢዎች እና 25 ተቆጣጣሪዎች መሳተፋቸውን የገለጹት፤  አቶ በለጠ፣ "ጥናቱ በየደረጃው ያሉ ፍርድ ቤቶች ያሉባቸውን ክፍተቶች ለይቶ የመፍትሄ ሃሳቦችን ያመላከተ ነው" ብለዋል።

ሳይንሳዊ ጥናቱ የፍርድ ቤቶች አሰራር ውጤታማነት፣ ተደራሽነት፣ ቅልጥፍናና ተገማችነት እንዲሁም ግልጸኝነትና መሰል መስፈርቶችን ላይ አተኩሮ የተካሄደ መሆኑንም አስረድተዋል።

"በየዘርፉ በተደረገ ጥናትም የተገልጋዮች እርካታ 65 በመቶ እንደሆነ በጥናቱ ለማረጋገጥ ተችሏል" ብለዋል።

የፍትህ ስርዓቱን እየተገዳደሩት ያሉ ሙስናና የቅሬታ ሰሚዎች የገለልተኝነት ችግሮች ሊስተካከሉ የሚገባቸው ጉዳዮች እንደሆኑ በጥናቱ መመላከቱን ገልጸዋል።

ፍርድ ቤቶች በአሰራራቸው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያልታገዙና የዳኞች የቁጥር ምጥጥንም አነስተኛ መሆኑን በጥናት መረጋገጡን ጠቅሰው፤ "ጥቅል የደንበኞች እርካታም መካከለኛ ደረጃ ላይ ነው" ብለዋል።

የተገልጋዩን እርካታ ወደ ከፍተኛና በጣም ከፍተኛ ለማምጣት እየተስተዋሉ ያሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ፈጥነው መስተካከል እንዳለባቸው የጥናት ውጤቱ ማመላከቱንም አቶ በለጠ አብራርተዋል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አብየ ካሣሁን በበኩላቸው ፤ በሳይንሳዊ መንገድ በተካሄደው ጥናት በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች የተገልጋዮችን የእርካታ ደረጃ ለማወቅ መቻሉን ገልጸዋል።

"በጥናቱ የተደረሰባቸው የስነ-ምግባር፣ የገለልተኝነትና የተደራሽነት ችግሮችን እንዲሁም በቴክኖሎጂ አለመዘመንና ሌሎችንም ክፍተቶችን ለማስተካከል ቀጣይ በትኩረት ይሰራል" ብለዋል።

በውይይት መድረኩ የከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶች፣ የተመረጡ የወረዳ ፍርድ ቤቶች አመራሮችና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም