ሁሉን ከአንድ ጓሮ!

415

በቀደሰ ተክሌ-(ኢዜአ)

ኢትዮጵያ 85 በመቶ ያህል ህዝቦቿ አርሶ አደሮች እንደሆኑ ይነገራል። ሰፊና ለም መሬትም አላት፡፡

ይሁን እንጂ የዜጎችን የምግብ ዋስትናን እንኳ ማስጠበቅ ባለመቻሉ ለስንዴ እጅ መዘርጋት ዘመናትን የተሻገረ ልምድ ሆኗል።

የኢትዮጵያ አፈር በአብዛኛው የሰጡትን የሚያበቅል ነው፤በዘመናዊ እርሻ ለማልማት በሁሉም ዘንድ አቅም ባይፈጠርም የዳልጋና የቀንድ ከብትን ጨምሮ የእንሰሳት ሀብት ልማትን በስፋት አካሂዶ ምጣኔኃብታዊ አቅምን ማጎልበት ይቻላል። ይህም የእርሻ በሬ ከማግኘት የዘለለ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አለው። በሀገራችን መስራት የሚችል የሰው ኃይልም በዛው ልክ ከፍተኛ ነው። በጥቅሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ማረስም፣ ማርባትም፣ማነብና  ሌሎችን በጥምር ለመስራት የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች አሉ። ነገር ግን "የዓባይን ልጅ ውሃ ጠማው" እንዲል ሀገራዊ ብሂሉ በእጃችን ጥቂት ብቻ ነገር ይዘን ከሰማይ ሌላ መና የምንጠብቅ መሆናችን ለትዝብት እየዳረገን ነው።

ሰፊ የእርሻ መሬት ኖሮት ዘምቢል ይዞ ገበያ የሚኳትን አርሶ አደር የበረከተባት ሀገር ሆናለች ኢትዮጵያ። የግጦሽ መሬት እና ሣር ታቅፎ እንደ ገና፣ፋሲካ፣አረፋ፣ ኢድ አልፈጥር ወዘተ የመሳሰሉ  ክብረ-በዓላት ሲመጡ በግ ለመግዛት ገበያ ገብቶ የሚጋፋው አሃዙ ቀላል አይደለም። ንብ በጓሮው እየዞረች የማር እሸት የሚናፍቀው ኢትዮጵያዊ ገበሬ ማየት ተገቢ ባይሆንም በእኛው ሀገር ተለምዷል። ነገሩን ካነሳን ላይቀር የፍራፍሬና የቅባት እህሎችን አይነት የማይለይ የአርሶ አደር ልጅ ቤት ይቁጠረው። የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ሲታይ ኢትዮጵያን ማደግ ባለባት ልክ እንዳታድግና የኑሮ ውድነት የሚታይባት ሀገር እንድትሆን አድርጓታል ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ይህን ያልነው ያለ መነሻ አይደለም። አርሶ አደር በአርሶ አደር ወግ ሲሰራ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በመገንዘብ ነው።ለዚህ ማሳያ  ሊሆኑ ከሚችሉ አርሶ አደሮች መካከል አቶ አብዱ አዳሜ አንዱ ናቸው።

አርሶ አደሩ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ካፋ ዞን የጊምቦ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። በሚኖሩበት የጡላ ቀበሌ የተለያዩ የግብርና ስራዎችን ይሰራሉ። እርሳቸው ከጨውና ከፋብሪካ ውጤቶች በስተቀር ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን መሰረታዊ ፍጆታ ለመግዛት ገበያ አይወጡም። ያርሳሉ፤ ያነባሉ፤ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬም ይተክላሉ። ከብት ማርባትም እንዲሁ የተሰማሩበት ስራ ነው። ከእነዚህ ጥምር የግብርና ሥራዎቻቸው ውስጥ የንብ ማነቡ ስራ እጅግ የላቀ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ያደረጋቸው  መሆኑን ይናገራሉ።

አርሶ አደር አብዱ እንዳሉት ከእርሻ ሥራቸው ጎን ለጎን በጓሯቸው የንብ ማነብ ሥራውን የጀመሩት በ1999 ዓ.ም በሦስት ባህላዊ ቀፎዎች ነው። ያኔ በዓመት ከአንድ የማር ቀፎ የሚያገኙት የማር መጠን በአማካይ ሦስት ኪሎ ግራም ብቻ ነው። የተሻሻሉ የንብ ቀፎዎችን መጠቀም ሲጀምሩ የሚያገኙት የማር ምርት መጠን እየጨመረ መጣ። በቂ የሆነ የንብ አበባ መቅሰሚያ አረንጓዴ ቦታ በማመቻቸት ዘጠኝ ዘመናዊ፣ 39 የሽግግር እና 48 የጨፈቃ የንብ ቀፎዎች አዘጋጅተው ንብ የማነብ ስራቸውን አጠናከሩ።

በአጠቃላይ በሦስት የንብ ቀፎዎች የጀመሩትን የንብ የማነብ ተግባር ዛሬ በ107 የንብ ቀፎዎች ላይ እያቀላጠፉት ነው። በዓመት በሁለት ጊዜ ቆረጣ ከሽግግር ቀፎዎች 1 ሺህ 326 ኪሎ ግርማ፣ ከጨፈቃ ቀፎ 1 ሺህ 536 ኪሎ ግራም እንዲሁም ከዘመናዊ ቀፎ 396 ኪሎ ግራም በጠቅላላ በዓመት 3ሺህ 258 ኪሎ ግራም ማር ያመርታሉ። ይህ የልፋት ዋጋቸው በዓመት ዳጎስ ያለ ገንዘብ ያስገኝላቸዋል። እንደ ማር ምርት ይዘት ከ200 ሺህ እስከ 250 ሺህ ብር በዓመት እንደሚያገኙ ይገልጻሉ። ያመረቱትን ማር በትስስር ለማዕከላዊ ገበያ በራሳቸው ያቀርባሉ።

አርሶ አደሩ ሌሎች አርሶ አደሮችም ፈለጋቸውን ተከትለው እንዲሰሩ ተሞክሯቸውን በማካፈል ያበረታታሉ፤ ይደግፋሉ። የንብ ቀፎዎችን  እንዲያዘጋጁ በማድረግ ካላቸው የንብ አውራ በመስጠትም ድጋፍ እያደረጉላቸው ነው። በዚህም ከ40 በላይ አርሶ አደሮች ከሰብል ምርት ሥራ ባለፈ በማር ምርት ላይ አትኩረው እንዲሰሩም አስችለዋል።

የአርሶ አደር አብዱን ፈለግ ተከትለው በዘርፉ ከተሰማሩት አርሶ አደሮች መካከል አቶ ይመር መኮንን አንዱ ናቸው። የንብ ማነቡን ስራ የጀመሩት አርሶ አደር አብዱ ከጀመሩ ከሁለት ዓመት በኋላ ነው። አርሶ አደር አብዱን አርዓያቸው አድርገው ሥራውን የጀመሩ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት 40 ያህል የንብ ቀፎዎች አሏቸው። ከአንድ የጨፈቃ ቀፎ እስከ 30 ኪሎ ግራም ማር እንደሚያገኙም ይናገራሉ።

አርሶ አደር ይመር ከተሰማሩበት የሰብል ምርት በተጨማሪ ማርና ቡና በማልማት ይጠቀማሉ። እንደ አርሶ አደር አብዱ ሁሉ እንደ ማንጎ፣ አቡካዶ፣ የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችና ፍራፍሬ ያሉ የግብርና ምርቶችንም በጓሯቸው ያመርታሉ።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ከክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በቅርቡ የእነዚህ ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች ማሳ ጎብኝተዋል። የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ሰፊም ይሁን ጠባብ የእርሻ ማሳ በአንድ አይነት የግብርና ምርት ብቻ መያዝ የለበትም። "አርሶ አደር ማለት ሰብል የሚያመርት ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የግብርና ምርት በጓሮው ማግኘት የሚችል ነው።" የአርሶ አደር አብዱን የግብርና ሥራ ተሞክሮ በቀጣይ ለሌሎች የክልሉ አርሶ አደሮች በማድረስ በርካታ መሰል አርሶ አደሮችን ለማፍራት በትኩረት ይሰራል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸው "ሀገራችን በምግብ ራሷን እንድትችል ከተለምዶ የአስተራረስና አመራረት ዘይቤ በመውጣት ተመጋጋቢ እርሻን መለማመድ ያስፈልጋል" ነው ያሉት። በሁሉም ዘርፍ የሚሰራና ውጤታማ የሆነ አርሶ አደር ለማፍራት በግብርናው ዘርፍ በኩል ድጋፍ እንደሚደረግም ነው የተናገሩት። የአካባቢው ወጣቶችም ነገን ተስፋ በማድረግ እንደ አቶ አብዱ ጠንክረው ሰርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ እንደ አርሶ አደር አብዱ አዳሜ ታታሪና የሰለጠነ ግብርናን አቀናጅቶ የሚከውን ዜጋ አጥብቃ ትሻለች። እኛም ይህን ተሞክሯቸውን መሬት ታቅፈው ረሃብ ለሚጠሩ ማንቂያ ይሆን ዘንድ አቀረብን።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም