በሐረሪ ክልል በህገ ወጥ መንገድ የተገነቡ ከ80 በላይ ቤቶች እንዲፈርሱ ተደረገ

433

ሐረር ፤ ሚያዚያ 03/2014 (ኢዜአ) የህግ የበላይነትን ለማስከበር በተካሄደው እንቅስቃሴ በህገ ወጥ መንገድ የተገነቡ ከ80 በላይ ቤቶች እንዲፈርሱ መደረጉን የሐረሪ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ሃላፊ አቶ ጥላሁን ዋደራ ዛሬ እንደገለጹት፤ እርምጃው የተወሰደው በቅርቡ በተካሄደው ህዝባዊ ውይይት በክልሉ የህግ የበላይነት እንዲከበር የቀረበው ጥያቄ ተከትሎ ነው።

በተለይ በክልሉ ህገ ወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ ተስፋፍቶ ይገኛል ያሉት ሃላፊው፤ ይህንን ለመከላከል የተጠናከረ ስራ መጀመሩን  አመልክተዋል።

ለዚህ ስራ በክልሉ ከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሰብሳቢነት ፖሊስ ኮሚሽን፣ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር መሬት ልማት፣ አቃቢ ህግና ደንብ ማስከበር በአባልነት የያዘ ግብረ ሃይል መቋቋሙን አስረድተዋል።

በዚህም የህግ የበላይነትን ለማስከበር በጋራ በተከናወነው ስራ እስካሁን በህገ ወጥ መንገድ የተገነቡ ከ80 በላይ ቤቶች እንዲፈርሱ መደረጉን አስታውቀዋል።

እርምጃ የተወሰደባቸው ቤቶች መንግስት ካሳ ከፍሎበት የሚገኝ መሬትና ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ በህገ ወጥ መንገድ የተገነቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ህገ ወጥ የመሬት ወረራና ቤት ግንባታ አርሶ አደሩንና መንግስትን በመጉዳት በአቋራጭ ለመበልጸግ የሚከናወን ወንጀል በመሆኑ የክልሉ መንግስት የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በአቋራጭ ለመበልጸግ የሚፈልጉ ህገ ወጥ ደላሎችም ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ ያሳሰቡት ሃላፊው፤ ህብረተሰቡም ህገ ወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ በመከላከል የድርሻውን እንዲወጣም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም