ኢትዮ-ቴሌኮም ከአምስት ድርጅቶች ጋር በአጋርነት መስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ

471

ሚያዚያ 03 ቀን 2014 (ኢዜአ)  ኢትዮ -ቴሌኮም የመደበኛ ባለገመድ ኢንተርኔት አገልግሎት በአጋርነት ከሚሰጡ አምስት ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ።

ኩባንያው ስምምነቱን የተፈራረመው 'ዌብ ስፕሪክስ አይቲ ሶሊሽን'፣ 'ዘርጋው አይ ኤስ ፒ'፣ 'ቪቫቴክ ትሬዲንግ'፣ 'ከዱሌ ቢዝነስ  ግሩፕ' እና 'ስካይ ኔት አይቲ ሶሊሽን' ከተባሉ ተቋማት ጋር ነው።

በስምምነቱ መሰረትም ኩባንያው ከተቋማቱ ጋር ለሶስት ዓመታት በጋራ ይሰራል፡፡

በዚህም ድርጅቶቹ የመደበኛ ኢንተርኔት ከፍተኛ ባንድዊዝ በመውሰድ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ለሚገኙ ደንበኞች አገልግሎት መስጠት ይችላሉ፡፡

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ እንደገለፁት፤ ስምምነቱ የአገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት ያስችላል ብለዋል።

በተጨማሪም ኢንቨስትመንትን ለማስፋትና የሀብት ብክነትን ለማስቀረት ጠቀሜታ እንዳለው አንስተው፤ ይህም ኢትዮጵያ  ለጀመረችው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እውን መሆን ሚናው የጎላ መሆኑን ነው ያብራሩት።

በመሆኑም በዘርፉ ከአጋር አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።

ኢትዮ-ቴሌኮም በአጋር ድርጅቶቹ አማካኝነት እስካሁን ከሃያ ሺህ በላይ ደንበኞችን ተጠቃሚ ማድረግ የቻለ መሆኑም ተመልክቷል።

ኩባንያው ከ400 ሺህ በላይ የመደበኛ ባለገመድ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞች ሲኖሩት እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2026 ቁጥሩን 3 ሚሊዮን ለማድረስ ውጥን ይዞ እየሰራ ይገኛል፡፡

የመደበኛ ኢንተርኔት አገልግሎቱን በመላ አገሪቱ ተደራሽ ለማድረግም እየተሰራ መሆኑ ተጠቅሷል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም