በመላ ኢትዮጵያ ሴቶች ጨዋታዎች የአትሌቲክስ፣ የእግር ኳስና መስማት የተሳናቸው ጠረጴዛ ቴንስ ውድድሮች ተደርገዋል

463

አዲስ አበባ ሚያዝያ 03/2014(ኢዜአ) በ4ኛው የመላ ኢትዮጵያ ሴቶች ጨዋታ ሶስተኛ ቀን ውሎ የአትሌቲክስ፣ የእግር ኳስና መስማት የተሳናቸው ጠረጴዛ ቴንስ ጨዋታዎች ተደርገዋል።

ዛሬ ከተደረጉት ጨዋታዎች መካከል የ5 ሺህ ሜትር ሩጫ ፍፃሜ አንዱ ሲሆን በዚህም ሰዓዳ አወል ከደቡብ ክልል አንደኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች።

በዚሁ ውድድር ጫልቱ ሹና ከኦሮሚያ ክልል ሁለተኛ፤ ድባቤ በየነ ከአዲስ አበባ ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል።

በጦር ውርወራ ፍፃሜ ውድድር ደግሞ ድንገቴ አዶላ ከኦሮሚያ ክልል አንደኛ፤ ብርሃኔ ቀጀላ ከሲዳማ ክልል ሁለተኛ፤ እንዲሁም የሺወርቅ አንማው ከአዲስ አበባ ከተማ ሶስተኛ በመሆን አጠናቀዋል።

ከፍፃሜ ውድድሮቹ በተጨማሪ የ800 ሜትር ሩጫ የማጣሪያ ውድድር ተካሂዷል።

ከአትሌቲክስ በተጨማሪ መስማት በተሳናቸው የጠረጴዛ ቴኒስ እና የእግር ኳስ ጨዋታዎችም ተደርገዋል።

መስማት በተሳናቸው የቡድን የጠረጴዛ ቴኒስ አዲስ አበባ ከተማ የወርቅ፤ ኦሮሚያ ክልል ብር እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ የነሐስ ሜዳልያ አሸናፊ ሆነዋል።

በእግር ኳስ ውድድር ሲዳማ ክልል ከድሬዳዋ ከተማ ጋር የተጫወቱ ሲሆን ሲዳማ ድሬዳዋን 6 ለ 0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

ስድስት ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች እየተካፈሉበት ያለው የሴቶች ስፖርታዊ ጨወታ እግር ኳስን ጨምሮ  በ10 የስፖርት አይነቶች በሀዋሳ ከተማ እየተከናወነ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም