ሴቶች፣ ሕጻናት እና አቅመ ደካሞችን ተጠቃሚ ለማድረግ በተከናወነው ሥራ ተስፋ ሰጪ ውጤት ተመዝግቧል- ሚኒስቴሩ

418

ሀዋሳ፤ ሚያዚያ 3/2014 (ኢዜአ) ሴቶች፣ ሕጻናትና አቅመ ደካሞችን ተጠቃሚ ለማድረግ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተከናወነው የተቀናጀ ሥራ ተስፋ ሰጪ ውጤት መመዝገቡን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ በሥሩ ያሉ ሴክተር መስሪያ ቤቶችን የ2014 የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም በሃዋሳ ከተማ እየገመገመ ነው።

በመድረኩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ሕጻናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ፣ በተለይ የሴቶች፣ የህጻናት፣ የአካል ጉዳተኞችና የአቅመ ደካማ ማህበረሰብ ክፍሎችን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም በየዘርፉ አሳታፊ የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ተዘጋጅቶ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ነው የጠቀሱት።

በተለይ እነዚህን ማህበረሰቦች በአግባቡ ተጠቃሚነታቸውን ማስጠበቅ የሚያስችል የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ እንዳሉት፤ መንግስት የሀገሪቱን የሰላም፣ የልማት እና የለውጥ ጉዞ ወደላቀ ከፍታ ለማሸጋገር በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ሴቶች፣ ሕጻናትና አቅመ ደካሞችን ተጠቃሚ ለማድረግ በተከናወነው  ቅንጅታዊ ሥራ ተስፋ ሰጪ ውጤት መመዝገቡን  ተናግረዋል።

ለእዚህም የሴቶችና ወጣቶችን እኩል ተሳትፎ ማረጋገጥ፣ የህጻናት መብትና ደህንነትን ማስጠበቅ፣ የስርዓተ ጾታ እኩልነትን ማስፈን፣ አካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን በተሻለ መልኩ ትኩረት እንዲያገኙ መደረጉን  ጠቅሰዋል።

በግምገማ መድረኩ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋትና በጉድለት የታዩትን በማረም በቀሪው ጊዜ የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ሁሉም ሀላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ አሳስበዋል።

የሰላም መደፍረስ በሰብአዊ ፍጡርና በልማት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ቢያሳድርም ቀዳሚ ተጎጂዎች ሴቶች፣ ሕጻናት፣ አረጋዊያን እና አካል ጉዳተኞች መሆናቸውንም ወይዘሮ አለሚቱ አንስተዋል።

ዘላቂ ሰላም እንዲሰፈን አፍራሽ ተልዕኮ ይዘው የሚንቀሳቀሱ አካላትን ሁሉም በጋራ በመታገል የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

የሲዳማ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ቢሮ ሃላፊ ወይዜሮ እመቤት ኢሳያስ፤  በአሁኑ ወቅት ሀገር በችግር ውስጥ ብትሆነም ማህበረሰቡን በመንቀሳቀስ በርካታ ተስፋ ሰጪ የልማት ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በቅርቡ በገጠመው የህልውና አደጋም ሴቶችና ወጣቶች የሀገር መከላከያ ሠራዊቱን በስንቅ ዝግጅትና በተለያዩ መልኩ ድጋፍ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጾ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

በተለይም ሴቶችን በልማት ማህበር በማደራጀት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው ከፍ እንዲል በተከናወነው ሥራ ስኬቶች መመዝገባቸውን ወይዘሮ እመቤት ተናግረዋል።

የሀገሪቱን አንድነት፣ ልማትና ሰላም በጠንካራ መሰረት ላይ ለማቆም የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በመድረኩ ሚኒስቴር ዴኤታዎች፣ የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የቢሮ ሃላፊዎች፣ የአካል ጉዳተኞች፣ የወጣቶች ማህበራት ፌዴሬሽኖችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም