የውጭ አገር ገንዘብ በፍተሻ የያዘ የፖሊስ አካል ገንዘቡን ይወስደዋል በሚል የሚናፈሰው ወሬ ፈፅሞ ሐሰት ነው

182

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 1/2014 ( ኢዜአ) "የውጭ አገር ገንዘብ በፍተሻ የያዘ የፖሊስ ወይም ሌላ የጸጥታ አካል ገንዘቡን ይወስደዋል" በሚል የሚናፈሰው ወሬ ፈፅሞ ሐሰት መሆኑን ፍትህ ሚኒስቴር ገለጸ።

በህገ-ወጥ መልኩ ከ100 የአሜሪካን ዶላር በታች ይዘው የሚገኙ ሰዎች ገንዘቡ ለመንግስት ገቢ ቢደረግም በወንጀል ግን ተጠያቂ እንዳይሆኑ የሚያደርግ አሰራር ተዘርግቷል።

በ1996 ዓ.ም የወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀጽ 346 በውጭ ሀገራት ገንዘብ መነገድን ወንጀል አድርጎ ተደንግጓል።

በተሻሻለው የብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 591/2000 ዓ.ም ተንተርሰው በመጡ የተለያዩ መመሪያዎች የውጭ ሀገራትን ገንዘብ በህገ-ወጥ መልኩ ይዞ የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ በወንጀል ተጠያቂ ይሆናል።

በውጭ ሀገራት ገንዘቦች መነገድን፣ መቀበልን፣ መስጠትን፣ ክፍያ መፈጸምን፣ መበደርን፣ ብድር መመለስን ጨምሮ ሌሎች ግብይቶችን መፈጸም በህግ የተከለከለ ነው።

ከውጭ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሰዎች ምን አይነት የገንዘብ አጠቃቀም ሊከተሉ እንደሚገባ በብሔራዊ ባንክ መመሪያ ቁጥር FXD/49/2017 አንቀጽ-3 በግልጽ ተቀምጧል።

በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ ኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተሯ ሃና ተኽልቁ፤ በተለያዩ አጋጣሚዎች በርካታ ሰዎች የውጭ አገር ገንዘቦችን በኪሳቸው ይዘው እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በተለይም በባቡር ጣቢያዎች፣ ኤግዚቢሽን ማዕከላትና በሌሎችም ቦታዎች ለህገ-ወጥ ግብይትና ሌሎችም ጉዳዮች ይዘው ይገኛሉ።

በመሆኑም በብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 591/2000 ዓ.ም አንቀጽ 26-መ በተቀመጠው የወንጀል ድንጋጌ መሰረት ተጠያቂ ይሆናሉ።

በወንጀሉ የተያዘው ገንዘብ ለመንግስት ገቢ የሚደረግ ሲሆን፤ ወንጀል ፈጻሚውንም በእስራት የሚያስቀጣው መሆኑን ምክትል ዳይሬክተሯ አስረድተዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ ከአንድ የአሜሪካን ዶላር ጀምሮ አነስተኛ የውጭ ሀገራት ገንዘብ በተለያዩ ምክንያቶች በኪሳቸው የሚይዙ ሰዎች መበራከታቸውንም ይጠቅሳሉ።

በመሆኑም በእነዚህ ሰዎች ላይ በአብዛኛው ክስ ለመመስረት የሚከለክል ድንጋጌ ባይኖርም፤ በአስተዳደራዊ እርምጃ ምላሽ እየተሰጠ ነው ብለዋል።

ከ100 የአሜሪካን ዶላር በታች ሰዎች በኪሳቸው ይዘው ሲገኙ ዶላሩን ለመንግስት ገቢ በማድረግ በወንጀል ተጠያቂ እንዳይሆኑ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ሂደት የውጭ ሀገር ገንዘቡን በፍተሻ የያዘው የፖሊስ ወይም ሌላ የጸጥታ አካል ለመንግስት ገቢ የሚያደርግበት አሰራር ተቀምጧል ብለዋል።

በብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 591/2000 ዓ.ም እና በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ መሰረት ዐቃቤ ህግ ገንዘቡ ለመንግስት ገቢ እንዲሆን ውሳኔ እንደሚሰጥም ተናግረዋል።

አሰራሩ የፍትህ ወይም ሌሎች የጸጥታ አካላት በዘፈቀደ የሰዎችን ገንዘብ እንዲወስዱ የሚያደርግ አለመሆኑንም አብራርተዋል።

በብሔራዊ ባንክ መመሪያ ቁጥር FXD/49/2017 አንቀጽ-3 መሰረት ሀገር ውስጥ ነዋሪ የሆነ ሰው የውጭ ምንዛሪ ባገኘበት ወይም ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ ለጉምሩክ ኮሚሽን ካሳወቀበት ቀን ጀምሮ ባሉት 30 ቀናት ውስጥ በባንኮች ወይም በህግ የውጭ ምንዛሪ አገልግሎት እንዲሰጡ በተፈቀደላቸው ተቋማት ቀርቦ ማስመንዘር ይኖርበታል።

በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ይዘው መንቀሳቀስ የሚችሉ የውጭ አገራት ነዋሪዎች ቪዛው በኢትዮጵያ ጸንቶ እስከሚቆይበት ጊዜ ድረስ ብቻ መሆኑም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም