ጨለማን ከማማረር---

467

በገዛኸኝ ደገፉ (ኢዜአ)

የብርሃን ጭላንጭል ዋጋ የገባቸው ጠቢባን “ጨለማን ከማማረር ቁራጭ ሻማ መለኮስ” በማለት ያመሰጥራሉ።  ዓለማችን በአንድም በሌላም ምክንያት በረሃብ አለንጋ እየተቀጣች ትገኛለች።

አንደኛውን ጨርሶ ሁለተኛ ወሩን ሊይዝ እየተንደረደረ ያለው የሩሲያና የዩክሬይን ጦርነት የአለማችንን የረሃብ ገበና አደባባይ አወጣው እንጂ አለማችን ጾሟን ውላ ማደሩን ከተያያዘችው ሶስትና አራት አመታት ማለፋቸውን ከሁለት ሳምንታት ቀደም ብሎ ለንባብ የበቃውና ስለችግሩና መፍትሄው ሃሳብ ያቀበለው የአለም ኤኮኖሚ ፎረም ድረገጽ ጽሁፍ እወቁት ብሏል።

በፈረንጆቹ 2020 የመንግስታቱ ድርጅት ያወጣውን ርሃብን የተመለከተ ሰነድ ያጣቀሰው ጽሁፉ በወቅቱ ከ720 እስከ 810 ሚሊየን አሊያም 10 በመቶ የሚሆኑት የአለም ሰዎች ከርሃብ ጋር ፊት ለፊት ሲፋለሙ እንደነበር ገልጾ የኮቪድ 19 መከሰት፣የአየር ለውጥ እንዲሁም በልዩ ልዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች የምግብ ችግሩን ከድጡ ወደ ማጡ ማድረጉን አስረድቷል።

በሁሉም ሃገራትና አህጉራት ግጭትና ረሃብ ላይነጣጠሉ የተሳሰሩ ከመሆናቸው የተነሳ የአንደኛው መከሰት ሌላኛውን መውለዱና አህጉር አቋራጭ ችግር መሆኑ ጥያቄ ውስጥ አይገባም በማለት ስለጉዳዩ ማብራሪያ የሰጡት የቀድሞው የቶጎ ጠቅላይ ሚኒስትር የአሁኑ የአለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ (IFAD) ፕሬዝደንት ጊልበርት ሆንግቦ የሩሲያና የዩክሬን ግጭት ስንዴና በቆሎን እንዲሁም የሱፍ ዘይትን ከስርጭት ውጪ በማድረጉ የምግብ ዋጋ ሰማይ ሲደርስ ረሃቡም በግልጽ መታየት ጀመረ ብለዋል።

የምግብ አቅርቦቱ እንዲሻሻልና ረሃብየሚያስቸግራቸው ሰዎች ቁጥር እንዲቀንስ ያስችላሉ ያላቸውን ተያያዥ የመፍትሄ አማራጮች የዘረዘሩት ፕሬዝዳንቱ ግጭት በሚበረታባቸው አካባቢዎች ሰብአዊ ድጋፍን ከሰላም ግንባታ ጋር ያስተሳሰሩ ፖሊሲዎች ወጥተው እንዲተገበሩ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገርና አካሄዶች ያሉትና የተሰባጠረ የምግብ አቅርቦት ስርአት እንዲዘረጋ ብሎም ኢ-እኩልነቶችን ትርጉም ባለው መንገድ የሚቀንሱ ድሃ ተኮር ስራዎች ሊተገበሩ እንደሚገባ ምክረሃሳባቸውን አቅርበዋል።

በሌላ በኩልም የገጠሩ አርሶ አደር የሚያመርተውን የሚጋራው የከተማው ማህበረሰብ የምርት ሂደቱ ባለድርሻ እንዲሆን የሚያስችሉ ዘመን አፈራሽ አሰራሮች ሊተገበሩ እንደሚገባ አጽንኦት በመስጠት ከተሜው ራሱ እያመረተ በቁጠባ እንዲጠቀም አስቻይ ሁኔታዎች ሲመቻቹለት የግድ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከከተሞች መስፋፋት ጋር በተያያዘ የእርሻ መሬት ማነስና የምርታማነት መቀነስ የመሳሰሉ ችግሮች መከሰታቸው እንደማይቀር በመገንዘብ ቀድመው የተዘጋጁ ቻይናን የመሳሰሉ ሃገራትና ከተሞቻቸው የዜጎቻቸውን እና የነዋሪዎቻቸውን የምግብ አቅርቦት ጥያቄ ሙሉ በሙሉም ባይሆን ትርጉም ባለው መልኩ ለመመለስ ራሳቸውን ከተቀናጀ የከተማ ግብርና ጋር በማስተዋወቅ የዘርፉ ፈርቀዳጆች ሆነዋል።

ቀደም ባሉት ጊዜያት ብዙዎች የከተማ ግብርና ሲባል የጓሮ አትክልት ብቻ ይመስላቸው እንደነበር ያብራሩት በቻይና የአካባቢና የእርሻ ጥበቃ ምርምር ማእከል ተመራማሪው ፕሮፌሰር ኪቻንግ ያንግ የሃገራቸው ግብርና ሚኒስቴር ከ40 በላይ የጥናትና ምርምር ተቋማትን በማደራጀት የከተማ ግብርና ላይ እንዲሰሩ ስለማድረጉና ጉዳዩ ብዙ አካላትን የሚያሳትፍ ጠቀሜታውም ሁለንተናዊ መሆኑን አስረድተዋል።

እንደ ፕሮፌሰሩ ማብራሪያ ዘርፉ ከሰዎች ምግብነት ባለፈ ለከተማ ሙቀት ቅነሳ፣ለእንስሳት መኖ አቅርቦት፣በካይ ጋዞችን ለማስወገድ የሚያደርገው አስተዋጽኦ ጉልህ ከመሆኑም በላይ የቤት ውስጥ እርሻ፣የከተማ ግብርና የግሪን ሃውስ ምህንድስና፣የእንጉዳይ ምርት፣ሃይድሮፖኒክስ(ያለ አፈር የሚሰራ የአትክልት ግብርና) እንዲሁም የሃይል ቁጠባ የመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት አስተዋውቋል ብለዋል።

“የከተማ ግብርና ሰፊ ቦታና ግብአት የማይፈልግ በመሆኑ ከተሜው ባለችው ትርፍ ጊዜ ከቤተሰቡ ጋር እየተዝናና ለራሱና የቤተሰቡ ፍጆታ አስቦ ስለሚያመርት ለተክሉ የቅርብ ክትትል ያደርግለታል፣ የኬሚካል ማዳበሪያና ጸረ ተባይ መድሃኒቶችን ስለማይጠቀም ሙሉ በሙሉ ተፈጥሮአዎ ምግብ ያስገኛል እንዲሁም ለምግብ ግዢ የሚያውለውን ገንዘብ ይቀንሳል” ያሉት ፕሮፌሰሩ “የቤትና የአጥር ግድግዳን ጨምሮ በቀላሉ በአካባቢያችን በሚገኙ ቁሳቁሶች ላይ የሚሰራ ተፈጥሮአዊ፣የስነምግብ ይዘቱ ያልተጎዳና በአጭር ጊዜ የሚደርስ በመሆኑ ተመራጭነቱ እያደገ ነው” በማለት አብራርተዋል።

የኢንዱስትሪዎች መበራከት የከተሞች መስፋፋትን ሲያስከትል የእርሻ መሬት መቀነስም አብሮ በመከሰቱ የአለማችን ከተሞች በኢንዱስትሪ ጭስ፣ በቤት ውስጥ ሙቀት ብሎም በመስታወት ነጸብራቅ መቃጠል ስለመጀመራ የሚያትቱት ሳይንስ ዳይሬክት ይፋ ያደረጋቸውየጥናት ሰነዶች እነዚህን በካይ ጋዞች ለመቀነስ፣የከተሞችን ሙቀት ቀዝቀዝ ለማድረግ ብሎም ለነዋሪዎቹ ሳምባ ንጹህ አየር ለማቅረብና የአይን ማረፊያና መንሸራሸሪያ ለማበጀት የከተማ ግብርና ተመራጭ መሆኑን ያሰምሩበታል።

የአሳ ማርቢያ ገንዳዎችን ጨምሮ የተለያዩ ከተማ ግብርና ተግባራት የሚከወንባቸው ቦታዎችና ግድግዳና ጣሪያቸው በአረንጋዴ ተክሎች የተሸፈኑ መኖሪያ ቤቶች ያላቸው ሙቀት ትርጉም ባለው ሁኔታ የቀነሰና ለነዋሪዎቻቸውም የተረጋጋ ስሜት በመፍጠር ኑሮን ስለማቅለላቸው ያስነበቡት የጥናት ውጤቶቹ ተክሎቹን ተከትለው የሚፈጠሩት የስነልቦናና የመንፈስ ጥንካሬዎች የነዋሪዎቹን የሆስፒታል ምልልስ በመቀነስ ቁጠባቸውን ከፍ ስለማድረጋቸው ጨምረው ዘርዝረዋል።

ጉዳዩ ከብዙ ቢሊየን የከተማ ነዋሪዎች ህልውና ጋር ቀጥተኛ ትስስር ያለው በመሆኑ ቸል ሊባል እንደማይገባውና ብዙም ባልታወቀበት ሁኔታ በአማካይ የአለማችንን 10 በመቶ የግብርና ምርት የሚያቀርብና አሜሪካ፣ ቻይና፣ ብራዚል፣ህንድ፣ሩሲያ፣ጀርመንና ጃፓን በስፋት እየተጠቀሙበት መሆኑ ያብራሩት የአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲው ተመራማሪ ማቲ ጂዮርጄስኩ ስራው በአፍሪካና በኤሽያ መለመድ ቢችል ጠቀሜታው ላቅ ያለ ነው ባይ ናቸው።  

“የከተሜውን ህይወት የከተማ ግብርና ያቀለዋል” በማለት ወደዚህ ስራ መግባታቸውን ለቢቢሲ አማርኛ ድረገጽ የተናገሩት የአፈር ጥበቃና የአዝርዕት ባለሙያው አቶ እስክንድር ሙሉጌታ በአዲስ አበባ በሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የተለያዩ ችግኞችን በማዘጋጀት ከመሸጣቸውም በተጨማሪ ድንች፣ ሽንኩርት እና ቲማቲም በማልማት በትምህርት ቤቶቹ ለሚካሄደው የተማሪዎች ምገባ መርሃግብር ላይም በጎ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

በኡጋንዳ፣በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና በደቡብ ሱዳን በግብርናው ዘርፍ መንግሥታዊ ባልሆነ ደርጅት ውስጥ ተቀጥረው መስራታቸው ከከተማ ግብርና ጋር እንዳስተዋወቃቸው ያልሸሸጉት አቶ እስክንድር “ኡጋንዳ ውስጥ በየጓሮው ባለው የበሬ ግንባር በምታክል ቦታ አትክልቶችን በመትከል ራሱን የሚመግብ ሕዝብ በርካታ ስለመሆኑ እማኝ ነኝ” ይላሉ።

 “የአውሮፓና አሜሪካ ከተሞች የህንፃቸዉ ጣራ ጠፍጣፋ ስለሆነ እንደ ቲማቲም፣ጎመን፣ሰላጣ፣ካሮት፣ ሃባብ፣ ወዘተ በቤታቸዉ ጣራ ላይ በማምረት ከራሳቸዉ ፍጆታ አልፈዉ ለሽያጭም የሚያቀርቡ የከተማ ገበሬዎች ብቅ እያሉ እንደሆነ” ማየታቸውን የገለጹት የግብርና ኢኮኖሚ ተመራማሪው ዘሪሁን ታደለ “በከተማ ግብርና የተለመዱትን የአትከልትና ፍራፍሬ ዓይነቶች ብቻ ሳይሆን እንደ እንጉዳይ የመሳሰሉትንም በማሳደግ የአመጋገብ ሥርዓታችንን ማስፋት ብቻ ሳይሆን እንደ ገቢ ምንጭነትም ልንጠቀምበት እንችላለን” ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።

ጉዳዩ ሁሉንም ሊያሳስብና ሊስብ እንደሚገባ አጽንኦት የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “የጓሯችን ስፋት ምንም ያህል ትንሽ ቢሆን ወይም ጓሮ ባይኖረን እንኳ፣ ከተሞቻችን ዕድገታቸውን ሲቀጥሉ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የተመጣጠነ አመጋገብን እውን ለማድረግ በቤት ውስጥ የጓሮ አትክልት ሥፍራዎች እንዲኖሩ ማድረግ የከተማ ግብርናን ለማጠናከር ወሳኝ ነው። በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ በሚውሉ ቁሳቁሶች አማካኝነት ወደላይ የሚዘረጉ የአትክልት ቦታዎችን መሥራት ለብዙኃኑ ቀላል ነው። ቤተሰቦች ይህንን የማድረግ ዐቅማቸውን እንዲፈትሹና እንዲጠቀሙበት አበረታታለሁ።” ሲሉ ለከተማ ነዋሪዎች ጥሪ አቅርበዋል።

የብርሃን ጭላንጭል ዋጋ የገባቸው “ጨለማን ከማማረር ቁራጭ ሻማ መለኮስ” እንዳሉት በከተሞች ካለው የህዝብ ቁጥር ጋር በተያያዘ የግብርና ምርት ፍላጎትና አቅርቦት ባለመጣጣሙ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ በሚገኘው ነዋሪ ላይ የኑሮ ውድነቱ ሰማይ ነክቶ ተፅእኖውን በማበርታቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ያመለከቱት ያልተሄደበት የከተማ ግብርና መንገድ ባያስጋልብም ከማዝገም ስለማያግድ በቁርጠኝነት ልንጓዝበት ይገባል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም