የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ለድርቅ ተጎጂ ወገኖች የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ

101

ጎባ ፤ መጋቢት 30/2014 (ኢዜአ) የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ለምስራቅ ባሌና ባሌ ዞኖች በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች 187 ኩንታል የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ።

በዩኒቨርሲቲው የሮቤና ሻሸመኔ ካምፓስ አመራሮች፣መምህራን፣ተማሪዎችና ሠራተኞች የተደረገው ይሄው ድጋፍ በምስራቅ ባሌ ዞን ዳዌ ሰረርና በባሌ ዞን መደ ወላቡ ወረዳ ለሚገኙ የድርቅ ተጎጂ ወገኖች እንደሚከፋፈል ተመልክቷል።

በመደ ወላቡና   ዳዌ ሰረር ወረዳዎች  በመገኘት ድጋፉን ያስረከቡት በዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ጎሳ ለማ ናቸው።

አቶ ጎሳ በወቅቱ፤ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራ በተጓዳኝ የህብረተሰቡን ችግርና ፍላጎት መሰረት ያደረገ የማህበረሰብ  አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ድጋፉ የተደረገው በድርቅ ሳቢያ ለችግር የተጋለጡ ወገኖች ለከፋ ጉዳት እንዳይጋለጡ ለማገዝ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሰቲው የህብረተሰቡን የድርቅ ተጋላጭነት ለመቀነስ የሚያደርገውን ድጋፍ ያጠናክራል ብለዋል፡፡

በባሌ ዞን የመደ ወላቡ ወረዳ የአደጋ ስጋትና የልማት ተነሺዎች ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ንጉሴ ከለለ ፤ በወረዳው በዝናብ እጥረት የተነሳ የተከሰተው የድርቅ አደጋ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግስት በመደበኛው የሴፍቲኔት መርሃግብር ከሚያደርገው ድጋፍ በተጓዳኝ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሕዝብና ድርጅቶች የሚያደርጉት የእህልና የእንስሳት መኖ ድጋፍ መቀጠሉንም ጠቅሰዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በምስራቅ ባሌ ዞን የዳዌ ሰረር ወረዳ ድርሻንም  አስረክቧል።

በሁለቱ የባሌ ዞኖች የዝናብ እጥረት ባስከተለው ድርቅ አርብቶ አደሮችና እንስሳት ለችግር መጋለጣቸውን  ከየዞኖቹ የአደጋ ስጋትና የልማት ተነሺዎች ጽህፈት ቤቶች የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም