በሶማሌ ክልል 260 ሄክታር መሬት የሚያለሙ የመስኖ ፕሮጀክቶች ተገንብተው አገልግሎት መስጠት ጀመሩ

93

ጅግጂጋ መጋቢት 30/2014(ኢዜአ) በሶማሌ ክልል ሊበን ዞን ሁለት ወረዳዎች 260 ሄክታር መሬት ማልማት የሚያስችሉ አራት የመስኖ ፕሮጀክቶች ተገንብተው አገልግሎት መስጠት ጀመሩ።

በዞኑ ዶሎ አዶና ቆልማዩ ወረዳዎች  የተገነቡት የመሰኖ አውታር ፕሮጀክቶቹ 51 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገባቸው  የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብዲቃድር  ኢማን  ገልጸዋል።

ኃላፊው እንዳሉት፤  ፕሮጀክቶቹ ከፊል አርብቶ አደር የሆኑ ከ1ሺህ በላይ  ቤተሰቦችን ተጠቃሚ የማድረግ አቅም ያላቸው ናቸው።

ከገናሌ ወንዝ በመጥለፍ የተገነቡት የመስኖ ፕሮጀክቶች ዋናው ካናል እና ንዑስ ማካፋፈያ ካናል ጨምሮ   አራት የውሃ ሞተሮችና የጎርፍ መከላከያ ባካተተ መልኩ መሰራታቸውን አስታውቀዋል።

ፕሮጀክቶቹ ግንባታቸው ባለፈው ዓመት ተጀምረው ዘንድሮ የተጠናቀቁ ሲሆን፤ በዞኑ የሚገኙ ከፊል አርብቶ አደር ነዋሪዎችን በመስኖ ልማት ተጠቃሚ በማድረግ  የነበረባቸው ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚያግዙ ናቸው።

በአሁኑ ወቅትም  ከፊል  አርብቶ አደሩቹ  የመስኖ አውታሮቹ ተጠቅመው የበቆሎ ሰብልና የተለያዩ አትክልቶችን ማልማት መጀመራቸውን  ኃላፊው አብራርተዋል። 

የሊበን ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ መሁመድ በበኩላቸው፤  በክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ የተገነቡ ፕሮጀክቶች በቆልማዩ ወረዳ መልካ ዲዳና ሰብላዩ ቀበሌዎች እንዲሁም በዶሎ አዶ ወረዳ ኮሌና ኩሊ ክሊምሳንጎ ቀበሌዎች  ከፊል አርብቶ አደር ነዋሪዎችን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚረዱ ናቸው ብለዋል።

ፕሮጀክቶቹ ዘጠኝ ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት ላይ በተዘረጋው “ካናል”   አማካኝነተ ሁለት መቶ ሥልሣ ሄክታር መሬት ማልማት  እንደሚያስችሉ  ተናግረዋል። 

በቄልማዩ ወረዳ የመልካ ዲዳ ቀበሌ ነዋሪ  አደን አህመድ ኢብራሂም  በሰጡት አስተያየት ፤

በአካባቢያቸው የተገነባላቸው የመስኖ አውታር  ቀደም ሲል የነበረባቸውን የውሃ እጥረት ችግር እንደሚፈታላቸው ገልጸዋል።

"የፕሮጀክቱ መገንባት ከገናሌ ወንዝ  ውሃ በጂሪካን እየቀዱ   አድካሚ የሆነ መንገድ በማቋረጥ  የሚያለሙት  የጓሮ አትክልት  በተሻለ ቅልጥፍና አስፋፍተው ይበልጥ  ለመጠቀም  ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው የተናገሩት ደግሞ  በዶሎ አዶ ወረዳ የኮሌ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ጄለው አሚን ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም