ከባድ የክረምት ዝናብ በሚፈጥረው "ላሊና" ምክንያት የሚከሰት የጎርፍ አደጋን ለመከላከል ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ ይገባል

354

መጋቢት 30 2014 (ኢዜአ) ከባድ የክረምት ዝናብ በሚፈጥረው "ላሊና" ምክንያት የሚከሰትን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ ይገባል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሰብሳቢነት የሚመሩት የተፋሰሶች ከፍተኛ ምክር ቤት ስብሳባ ዛሬ ተካሂዷል፡፡

ሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም የሚመለከታቸው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የበላይ ኃላፊዎች የተካተቱበት ምክር ቤት የጎርፍ አደጋን በመከላከል፣ እንቦጭን በማስወገድና በአረንጓዴ አሻራ ዙሪያ ተወያይቶ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

በዚህም በኢትዮጵያ ካሉት 12ቱ ዋና ዋና ተፋሰሶች ከአዋሽ ተፋሰስ ውጭ በሌሎች አካባቢዎች በቂ የተፋሰስ ሥራ እንዳልተከናወነ ተገልጿል፡፡

የስምጥ ሸለቆ ሀይቆችና የአባይ ተፋሰስ ላይ የሚከናወኑ የተፋሰስ ሥራዎች በመጠናቀቅ ላይ ሲሆኑ የኦሞ ጊቤ፣ ዋቢ ሸበሌና ገናሌ ዳዋ ተፋሰሶች ላይ ግን በጅምር ላይ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የተፋሰስ ሥራዎች ወቅታቸውን ጠብቀው ሙሉ በሙሉ ካልተጠናቀቁ በቀሪዎቹ ብቻ ሳይሆን የተሰሩትንም ጭምር የሚያበላሹ በመሆናቸው በቂ ትኩረት እንዲደረግም  ነው ተሳታፊዎቹ የጠየቁት፡፡

በደቡብ ክልል የዳሰነች ማህበረሰብ በጊቤ ሰው ሰራሽ ሀይቅ እንዲሁም በአፋር ክልል በአዋሽ ወንዝ ምክንያት ጉዳት እየደረሰ በመሆኑ ፈጣን ምላሽ እንደሚያስፈልገውም እንዲሁ፡፡

የባሮ ወንዝ ለጋምቤላ ከተማ ስጋት እንደሆነ ቀጥሏል፤ከጊቤ ሦስት ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የሚለቀቅ ከፍተኛ ውሃም ትምህርት ቤቶች ጤና ተቋማትን አውድሟል፤ በአንድ ዓመት ብቻ ከ117 ሺህ በላይ የቤት እንስሳትም በዚሁ ምክንያት መሞታቸውንም ገልጸዋል፡፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የጊቤ ሦስት ኃይል ማመንጫ ሰው ሰራሽ ግድብ አካባቢ የተከሰተ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ከ110 ሺህ በላይ ዜጎችን ተረጂ እንዲሆኑ ማድረጉንም ጠቁመዋል፡፡

የጣና በለስ ፕሮጀክትም ከ15 ሺህ በላይ አሳ አስጋሪዎችን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በቀጥታ ተጎጂ እያደረጋቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ በበኩላቸው፤ የጎርፍን አደጋ ለመከላከል የሚሰሩ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ከክልል ማዕቀፍ መውጣት አለባቸው ብለዋል፡፡

አንድ ተፋሰስ ሁለትና ከዚያ በላይ ክልሎችን የሚያስተሳስር በመሆኑ የክልሎች የጋራ ትብብር መኖር አለበት ብለዋል፤ ለአብነት የአዋሽ ተፋሰስ የአፋር፣ ኦሮሚያና አማራ ክልሎችን እንደሚያስተሳስር በመግለጽ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የላሊና ወቅት ስለሆነ በመጭው ክረምት ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም በ12ቱ ዋና ዋና ተፋሰሶች በንዑስ ተፋሰሶች ጭምር ሁሉንም ያሳተፈ የተፋሰስ ልማትና የጎርፍ መከላከል ሥራ ማከናወን ይገባል ብለዋል፡፡

"የአዋሽ ተፋሰስን ጨምሮ በሁሉም አካባቢዎች በቂ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራ መሥራት፤ ሥራውን መከታተልና በቂ ምላሽ መስጠት ይገባል" ብለዋል።

በሚሊዮን የሚቆጠር ተፈናቃይ ባለበት አገር በጎርፍ ምክንያት ተጨማሪ ተፈናቃይ መኖር የለበትም ነው ያሉት፡፡

ለአብነት ትናንት በጦርነት ሲታመስ የነበረው የአፋር ህዝብ ዛሬ ደግሞ በአዋሽ ወንዝ ጎርፍ እንዲጠቃ መፍቀድ የለብንም ብለዋል፡፡

ባለፈው ዓመት የጎርፍ አደጋን በመከላከል ረገድ የተሻለ ሥራ መከናወኑን ጠቅሰው፤ አሁንም ያለንን አቅም አሟጠን አደጋው ከመከሰቱ በፊት የቅድመ-ጎርፍ መከላከል ላይ ማተኮር አለብን ብለዋል፡፡

የክልል መንግስታት የፌዴራል መንግስትን ብቻ ከመጠበቅ ይልቅ ማህበረሰቡን በማስተባበር ተጨማሪ የፋይናንስ አቅም መፍጠር እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

የተፈጥሮ ሃብታችንን በማልማት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የውሃ አካላት ዳርቻ ህግ በፍጥነት እንዲጸድቅ ጥረት እናደርጋለን፤ እስከዚያው ግን ባለን አቅም መሥራት አለብን ብለዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ጎርፍን ለመከላከልም ሆነ ለአካባቢ ልማት ወሳኝ በመሆኑ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር አማካኝነት በኢትዮጵያ በአራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ 20 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል  እቅድ ተይዞ በሦስቱ ዓመታት 17 ነጥብ 3 ቢሊየን ችግኝ ተተክሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም