የፌዴራል ዋና ኦዲተር የኦዲት ግኝቶችን ለሚዲያ የማሳወቅ ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል

199

አዲስ አበባ መጋቢት 30/2014(ኢዜአ) የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ስለኦዲትና የኦዲት ግኝቶች ለሚዲያ የማሳወቅ ሥራ መሥራት እንዳለበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የ2014 ዓ ም በጀት ዓመት የስድስት ወር ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ማብራሪያ አድምጧል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ በዚህ ጊዜ እንደገለጹት፤ ተቋሙ የኦዲት ግኝት ያለባቸውን ተቋማት ለሚዲያ በማሳወቅ ህብረተሰቡና የሚመለከታቸው አካላት እንዲገነዘቡ ማድረግ ይጠበቅበታል።

ኦዲት ተደራጊ መሥሪያ ቤቶች የኦዲት ግኝት በተደጋጋሚ በሚዲያ ሲገለጽ ለአስፈጻሚው አካል ተፅዕኖ መፍጠሪያ አጋጣሚና ለጥቆማ የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

ኦዲትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በሚዲያ ሲገለጽ ኅብረተሰቡ ሞጋችና ባለቤት እንዲሁም ተቋማትም ተአማኒና ተቀባይነት ያላቸው የሕዝብ ተቋማት ሆነው እንዲቀጥሉ የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።

በመሆኑም መሥሪያ ቤቱ ከዚህ ቀደም ለተቋማት ብቻ ከሚያቀርበው ሪፖርት ጎን ለጎንም ለመገናኛ ብዙሃን ጭምር የመስጠትና የማሰራጨት ሥራ እንዲሰራ ጠቁመዋል።  

የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በኦዲት ክዋኔ፣ በሂሳብ አያያዝ፣ በአሰራርና በአደረጃጀት ምሣሌና የልህቀት ማዕከል መሆን እንደሚጠበቅበትም አቶ ክርስቲያን ገልጸዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አራሬ ሞሲሳ በበኩላቸው የስድስት ወር ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት የዋናውን መሥሪያ ቤት የሚገልጽና ደረጃውን የጠበቀ መሆን እንደነበረበት ገልጸዋል።

የዋና መሥሪያ ቤት የስድስት ወር ዕቅድ አፈጻጸም ችግሮቹን ማየቱ በጎ ጎን መሆኑን ገልጸው ይህም ለወደፊቱ ለማሻሻል ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ምክትል ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሰረት ዳምጤ ቋሚ ኮሚቴው ያነሳቸው ራሳቸውን በደንብ እንዲያዩ ያደረጋቸው በመሆኑ የሪፖርት መዘግየትን ለወደፊቱ እንደሚያስተካክሉ ገልጸዋል።

አቶ ክርስቲያን በተጨማሪም በቋሚ ኮሚቴ አባላት በተነሱት ሀሳቦች መሠረት መሥሪያ ቤቱ እስከ ሚያዚያ 5 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ የተስተካከለ የአፈጻጸም ሪፖርትና ዕቅድ እንዲያቀርብ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም