አገር-ዓቀፍ የፍልሰት ፖሊሲ ዘንድሮ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል

134

መጋቢት 30 2014(ኢዜአ) የፍልሰት ጉዳይ በተቀናጀ መንገድ የሚመራ አገር-ዓቀፍ የፍልሰት ፖሊሲ ዘንድሮ ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ፍትህ ሚኒስቴር ባዘጋጀው አገር አቀፍ የፍልሰት ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ከተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲዎችና መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ካደረጉ ኤምባሲ ተወካዮች ጋር ተወያይቷል።

ፖሊሲው ለሥራ ወደ ውጭ አገር የሚሄዱ ዜጎችን፣ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ሰዎችን በህገ-ወጥ መንገድ የማሻገር ወንጀል እንዲሁም የድንበር አስተዳደርና ቁጥጥር ሥርዓትን ጨምሮ በሰባት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ የተዘጋጀ ነው።

በፍትህ ሚኒስቴር የብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ፈትያ ሰኢድ፤ የፍልሰት ፖሊሲው ቀደም ሲል በተለያዩ ፖሊሲዎች ያልተካተቱና ተካተውም ትኩረት ያስፈልጋቸዋል የተባሉ ጉዳዮችን የያዘ መሆኑን አብራርተዋል።

ለሥራ ወደ ውጭ አገር የሚሄዱ ዜጎች፣ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ከሌሎች አገሮች ወደ ኢትዮጵያ በጥገኝነት የሚመጡ ዜጎችን የሚመለከቱ ጉዳዮች በተበታተነ መልኩ ሲከናወኑ መቆየታቸውንና ፖሊሲው በተበታተነ መልኩ ሲከናወኑ የነበሩ ተግባራትን በተቀናጀ አግባብ ለመምራት እንደሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

ዜጎች ለተሻለ የኑሮ ፍለጋ  ከአገር በሚወጡበት ወቅት ደህንነታቸውና ሰብዓዊ መብታቸው ለአገር አስተዋጽኦ የሚያደርጉበት ሁኔታም በአግባቡ ይመራል ያሉት ሃላፊዋ፣ ፍልሰተኞችን ከመጠበቅ፣ ድጋፍ ከማድረግ፣ ተመላሾችን መልሶ ከማቋቋም አንጻርም ረቂቅ ፖሊሲው ተቃኝቷል ባማት አስረድተዋል።

በረቂቅ ፖሊሲው ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት መደረጉን የተናገሩት ኃላፊዋ ፈትያ ሰኢድ፤ በዚህም ፖሊሲው የተገኙ ግብዓቶችን በማካተት በዘንድሮው ዓመት ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ አገራት ኤምባሲ ተወካዮች፣ የተባበሩት መንግስታት ተወካዮችና ሌሎች ተሳታፊዎች በረቂቅ ፖሊሲው መታየት አለባቸው ያሏቸውን ጉዳዮች አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ፖሊሲውን ተግባራዊ ለማድረግ  ለምታከናውነው ተግባር አጋርነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በውይይቱ የተሳተፉ የዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ኤምባሲዎች አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም