በ"ኦንላይን" የንግድ ምዝገባና ፍቃድ የአስራር ሥርዓት ከመጪው ሐምሌ ወር ጀምሮ ለመተግባር ዝግጅት እየተደረገ ነው

258

ጂግጂጋ ፤መጋቢት 30/2014 (ኢዜአ) የ"ኦንላይን" የንግድ ምዝገባና ፍቃድ የአሰራር ሥርዓት ከመጪው ሐምሌ ወር ጀምሮ በመላው ሀገሪቱ ለመተግበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።

አሰራሩን  ለማስተዋወቅ በሚኒስትሩ የተዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በሱማሌ ክልል ጂግጂጋ ከተማ ተካሄዷል።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሐመድ  በመድረኩ  ላይ እንዳሉት፤በ"ኦንላይን" የሚደረግ የንግድና ምዝገባና ፍቃድ የደንበኞችን ምልልስ በማስቀረት በተቋማት መካከል ቅንጅታዊ አሰራርን  ያዳብራል።

በሀገራችን ንግድ ለመጀመር  ያለውን አመቺነት በማሳደግ ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ሀገራችን ለውጭ ኢንቨስትመንት ተመራጭ  ያደርጋታል ብለዋል።

 “በሀገሪቱ  የንግድ ስራ ለመጀመር 32 ቀናት ይፈጅ የነበረውን ወደ አምስት ቀናት በማሳጠር የተገልጋዮችን እርካታ እንደሚያሳድግ እንዲሁም ጊዜና ወጪን እንደሚቆጥብ ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

አሰራሩ ከመጪው  ሐምሌ ወር ጀምሮ በመላው ሀገሪቱ ተግባራዊ ለማድረግ በንግድ ዘርፍ የተሰማሩ አመራሮችና ባለሙያዎች ግንዛቤ የማስጨባጥ ስራ እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል።

እስካሁንም  ከ1ሺህ አምስት መቶ በላይ የዘርፉ ባለሙያዎች መሰልጠናቸውን ጠቅሰዋል።

የሶማሌ ክልል ንግድና ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ መርዎ አብዲአዚዝ በበኩላቸው፤   በክልሉ የ"ኦንላይን " ንግድ ምዝገባና ፍቃድ አሰጣጥ  በሙከራ ደረጃ  ለመጀመር ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።

"በክልል ደረጃም በአሁኑ ወቅት በዘጠኝ ከተሞች ተወስኖ ያለውን የሙከራ አገልግሎት ወደ ሌሎች ኢንተርኔትና  መብራት አገልግሎት ያለባቸው የከተማ አስተዳደር ፣ የዞን እና የወረዳ ከተሞች ለማስፋፋት ይሰራል" ብለዋል።

በማስተዋወቂያ መመድረኩ ላይ ከሶማሌ ፣ ከኦሮሚያ፣ ከሐረሪ ክልሎችና ድሬዳዋ  አስተዳደር የተውጣጡ  የንግድ ዘርፍ አመራሮች መሳተፋቸውን ኢዜአ ከጂግጂጋ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም