መሠረታዊ የምጣኔ ሀብት ለውጥ ለማምጣት በግብርና የሚባክነውን ምርት መታደግና ዘርፉን በቴክኖሎጂ ማገዝ ያስፈልጋል

265

መጋቢት 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ መሠረታዊ የምጣኔ ሀብት ለውጥ ለማምጣት በግብርናው ዘርፍ የሚባክነውን ምርት መታደግና ዘርፉን በቴክኖሎጂ ማገዝ ወሳኝ እርምጃ መሆኑ ተመላከተ።

ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ አመታዊ የግብርና ኢኖቬሽን የምክክር መድረክ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ በግብርና ሥራ ተሰማሩ አካላትና የመንግስታዊ ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት አካሂዷል፡፡

በመድረኩ ላይ የምግብ ፍላጎትን በራስ አቅም ለመሸፈን በግብርናው ላይ ከመንግስት በተጨማሪ የግሉ ዘርፍ እንቅስቃሴ የማይተካ ሚና አለው ተብሏል።

ግብርናውን የሚያሳልጡ የፈጠራ ውጤቶችና የገበያ ትስስር መፍጠር ወሳኝ መሆኑ የተነሳ ሲሆን ሀገር በቀል የሆኑ እውቀቶች ላይ ቴክኖሎጂን በማከል የግብርናውን ዘርፍ በከፍተኛ ሁኔታ ውጤታማ ማድረግ እንደሚቻል ነው የተገለጸው።

በዚህ ወቅት የፐርፐዝ ብላክ የግብርና ዳይሬክተር ዶክተር ኤርሚያስ ነሲቡ እንደገለጹት በኢትዮጵያ የግብርና ስነ-ተግባቦትና የቴክኖሎጂ ስርዓት ማዕከል በማቋቋም ግብርናን በቴክኖሎጂና በፈጠራ ክህሎት ማሳደግ አሰፈላጊ ነው።

May be an image of 7 people, people sitting and indoor

ግብርናን ቀልጣፋና ዉጤታማ እንዲሁም ቀጣይነት ያለዉ የልማት ምንጭ ለማድረግ ቴክኖሎጂና ፈጠራን አክሎ መስራት እጅግ አስፈላጊ ነው ሲሉ አመልክተዋል፡፡

በቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ስሜነው ከስክስ በግብርናው ዘርፍ የሚሰሩ የግብርና ፈጠራዎች ለዘርፉ እድገት ወሳኝ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።

ግብርናው የተለያዩ ችግሮችን ፈቺ በመሆኑ በዘርፉ ላይ የሚከናወኑ ቴክኖሎጂያዊ ፈጠራዎች ልዩ ትኩረት የሚያሻቸው ናቸው ብለዋል።

የፐርፐዝ ብላክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ፍሰሃ እሸቱ በበኩላቸው "80 በመቶ በላይ የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል ግብርና ላይ መሰረት ያደረገ ነው፣ በዚህም መሰረታዊ የምጣኔ ሀብት ለውጥ ለማምጣት ካስፈለገ የሚባክንን ምርት መታደግና ግብርናን በቴክኖሎጂ ማገዝ አማራጭ የሌለዉ መፍትሄ ነው" ብለዋል።

ዘርፉን በቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ማገዝ ለስራ እድል ፈጠራ፣ ለገበያ ትስስርና ሰፊ መሬትን ለግብርና ለማዋል ያግዛል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም