ሕገ-ወጥ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራትን ትስስር ማጠናከር ይገባል

115

መጋቢት 30 ቀን 2014- (ኢዜአ) ሕገ-ወጥ የንግድ ተግባራትን የሚፈጽሙ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር የሸማቾች መብት ጥበቃ ላይ የተሰማሩ ተቋማት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ተቋማቱ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪና ሌሎች ሕገ-ወጥ ተግባራትን የሚፈጽሙ ነጋዴዎችን ለመከላከል ከማስተማር ባለፈ አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በሸቀጦች ላይ እየታየ ላለው የዋጋ ንረት ዓለምአቀፍ ጫናዎች፣ የምርትና አቅርቦት አለመመጣጠን እንደ ምክንያት የሚጠቀስ ቢሆንም፤ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ድርሻ እንዳላቸው በምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይገለጻል።

የምጣኔ ኃብት ባለሙያው አቶ ደረጀ ደጀኔ እንደገለጹት፤ ከዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት በተጨማሪ የሕገ-ወጥ ነጋዴዎች የምርት ስወራና ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሸቀጦች ላይ እየተስተዋለ ላለው የዋጋ ንረት ምክንያት ነው።

የወጪና ገቢ ንግድ አለመመጣጠንም ለዋጋ ንረት ምክንያት መሆኑንም አንስተዋል።  

በኢኮኖሚ አሻጥር የሚከሰተውን የዋጋ ንረት ችግር ለመፍታት በየአካባቢው ያሉ የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ራሳቸውን በማጠናከር ምርትን በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ከማቅረብ ባሻገር የሸማቹን መብት ለማስከበር መሥራት አለባቸው ብለዋል።

ለሸማቾች መብት ጥበቃ የተቋቋሙ የሲቪክ ማኅበራትም ነጋዴውንና ሸማቹን ኅብረተሰብ በማስተማር ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ  ቁምላቸው አበበ በበኩላቸው፤ ለዓመታት ኅብረተሰቡን እየፈተነ ላለው የዋጋ ግሽበት መፍትሄ ለማቅረብ ድርጅቱ በግንቦት ወር 2013 ዓ.ም መቋቋሙን አስረድተዋል።

ድርጅቱ በመገናኛ ብዙኃን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው፤ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት ለመፈረም መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የፀረ-ውድድር ተግባር ቁጥጥር የምርመራ ክስ ክፍል የሕግ ባለሙያ ጌትነት አሸናፊ በበኩላቸው፤ ከኮሮና ወረርሽኝና የፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ በሰብል ምርትና በግንባታ እቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ መስተዋሉን ተናግረዋል።

በአቅርቦት እጥረት ሳቢያ የተከሰተና ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ያለው የዋጋ ጭማሪ እንደተፈጠረ ሁሉ አጋጣሚውን  በመጠቀም በሥምምነት በሚመስል መልኩ ዋጋ መጨመር የሚታይበት ሁኔታ መኖሩንም አስረድተዋል።

ይህንን ተከትሎ በተለያዩ ክልሎች ንግድ ቢሮ ያላግባብ ዋጋ ጭማሪና ምርት ማከማቸት ላይ በተሰማሩ ነጋዴዎች  እርምጃ መወሰዱንም ገልጸዋል።

ከዚህ ባሻገር በቅርቡ ጭማሪ በተስተዋለባቸው የግንባታ ግብአቶችና የምግብ ምርቶች ላይ የተደረገው የዋጋ ጭማሪ ምክንያት እየተጣራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በሕገ-ወጥ ተግባር የሚሰማሩ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላትን በሚመለከት ሸማቹ ለህግ አካላት ማሳወቅና ከመንግሥት ጋር ተባብሮ መሥራት አለበትም ብለዋል።

የንግዱ ማኅበረሰብም በሕገ-ወጥ ተግባራት መሳተፍ እስከ ሰባት ዓመት ጽኑ እሥራት የሚያስቀጣ መሆኑን በመገንዘብ ከመሰል ተግባራት ራሱን ማራቅ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም