በህገ-ወጥ መንገድ የተያዙ የቀበሌ ቤቶችን ለአቅመ ደካሞች ሊሰጥ ይገባል - የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች

56
አምቦ ነሃሴ 30/2010 በህገ-ወጥ መንገድ የተያዙ የቀበሌ ቤቶችን በማስመለስ ለአካል ጉዳተኞችና አቅመ ደካሞች ሊሰጥ እንደሚገባ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ። የከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ በህገ-ወጥ መንገድ የተያዙ የቀበሌ ቤቶችን በማስመለስ ለሚገባው ሰው  ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በአምቦ ከተማ የ02 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አያንቱ ሚኒሻ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በከተማው የግለሰብ ቤት ተከራይተው ለመኖር የማይችሉ በርካታ አካል ጉዳተኞች፣ አቅመ ደካሞችና ሴቶች በከፋ ችግር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በከተማው የሚገኙ በርካታ የቀበሌ ቤቶች ደግሞ የግል መኖሪያ ቤት ባላቸውና እራሳቸውን ማስተዳዳር በሚችሉ እንዲሁም በህገወጥ መንገድ ቤቱን ሰብረው በገቡ ሰዎች ተይዘው እንደሚገኙ ገልፀዋል። ስለዚህም በከተማው በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ የቀበሌ ቤቶችን በማስመለስ በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን የቤት ባለቤት ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ የ01 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ታደሠ ተሾመ በበኩላቸው የቀበሌ ቤቶቹን በአመራሮችና የአመራር ቤተሰቦች እንዲሁም የግል ቤታቸውን አከራይተው በሚጠቀሙ ግለሰቦች የተያዙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በከተማዋ አካል ጉዳተኞችና አቅመ ደካሞች እንዲሁም የኤች አይ ቪ ኤድስ ህሙማን በቤት ኪራይ መናር ምክንያት እየተሰቃዩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም መንግስት ቤቶቹን ለይቶ በማስመለስ ለሚገባቸው ሰዎች ሊሰጥ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡ እሳቸውም የአከባቢውን ነዋሪዎች በማስተባባር በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ ቤቶችን በማጋለጥ በኩል የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ አረጋግጠዋል፡፡ የአምቦ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቀነኒ ወርቁ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ በከተማው በህገ ወጥ መንገድና በጉልበተኞች የተያዙ በርካታ የቀበሌ ቤቶች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ ይህም በህብረተሰቡ ዘንድ የረጅም ጊዜ የመልካም አስተዳዳር ጥያቄ ሆኖ መቆየቱንም ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜም ይህን የረጅም ዓመት የህዝብ ጥያቄ ለመፍታት በስድስቱም ቀበሌ ኮሚቴ በማዋቀር የሁሉንም የቀበሌ ቤቶች አያያዝ የማጣራትና የመመርመር ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ህብረተሰቡም ከኮሚቴው ጎን በመቆም ያለውን ሁሉ መረጃ እንዲያደርስ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በህገ ወጥ መንገድ የቀበሌ ቤቶችን ይዘው የሚገኙ ግለሰቦችም አስቀድመው ካላሳወቁ ቤቱን ከመነጠቅ ባለፈ በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ ባሳለፍነው በጀት ዓመትም በህብረተሰቡ ጥቆማ አማካኝነት በህገወጥ መንገድ የተያዙ 53 የቀበሌ ቤቶችን የመለየት ስራ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡ በአምቦ ከተማ ከ1 ሺህ በላይ የቀበሌ ቤቶች መኖራቸውን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም