ኢትዮጵያ ከሁሉም አገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር ጽኑ ፍላጎት አላት

110

መጋቢት 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከሁሉም አገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር ጽኑ ፍላጎት እንዳላት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

መንግሥት ለሰብዓዊ ድጋፍ ሲባል የወሰነው የግጭት ማቆም እርምጃ ለሰብዓዊ ጉዳዮችና ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋገጠ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከኮቪድ-19 ወረረሽኝ በኋላም አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በለኮሰው ጦርነት፣ በተወሰኑ አካባቢዎች በተከሰተ ድርቅና በሌሎች ውጫዊ ጫናዎች ፈርጀ ብዙ ፈተናዎች ተጋርጠውበታል።

ይሁንና መንግሥት የአገሪቷን ሉዓላዊነትና የሕዝቡን ደህንነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው፤ በችግር ላይ የወደቁ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ላደረጉት የሰብዓዊ ድጋፍ አመስግነዋል።

የዜጎች ሕይወት ጉዳይ በመሆኑ መንግሥት በትግራይም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ለአገሪቷ ዘላቂ ሰላም ብሔራዊ ምክክር ለማካሄድ እየሰራ መሆኑን አብራርተው፤ ጦርነቱ በተካሄደበት ሥፍራዎች የተፈፀሙ ሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን አጣርቶ የወንጀል ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በዚህም ቀደም ብሎ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በጋራ ባካሄዱት ምርመራ መሰረት በሁሉም ወገን ያሉ የመብት ጥሰት የፈፀሙ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ኮሚቴ አቋቁሞ ሲሰራ መቆየቱ አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ ከሁሉም አገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከርና የውስጥ ሰላም ለማረጋገጥ ፅኑ ፍላጎት እንዳላት ገልፀው፤ ያም ሆኖ በአንዳንድ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኩል ጥረቷን ያለማክበርና ዕውቅና የመንሳት አዝማሚያዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

በቅርቡ መንግሥት የወሰነው የሰብዓዊ ግጭት ማቆም ውሳኔም መንግሥት ላልተገደበ ሰብዓዊ እርዳታና ሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያረጋገጠበት መሆኑን ተናግረዋል።  

ሰሞኑን በአምነስቲ ኢንተርናሽናልና በሂዩማን ራይት ዎች የወጣው ሪፖርት የአንድ ወገን የፖለቲካ ፍላጎት የተንፀባረቀበትና ነባራዊ ዕውነታውን የማያሳይ በመሆኑ መንግሥት እንደማይቀበለውና ቅሬታውን እንደገለፀ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ነፃና ገለልተኛ ተቋም እንደሆነ ገልፀው፤ ኮሚሽኑ የሚያወጣቸውን ተጨባጭ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርቶችን ተዓማኒነት በመካድ የሚገልጹ አካላትን ኮንነዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም