ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተሳተፉበት የሳይንስና ቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ በሀዋሳ ተከፈተ

435

ሀዋሳ ፤ መጋቢት 29/2014 (ኢዜአ) በሀዋሳ ከተማ የሚገኙ 45 የመንግስትና የግል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተሳተፉበት የሳይንስና ቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ ዛሬ ተከፈተ።

"ትምህርት ቤቶቻችንን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ማዕከላት በማድረግ የሀገራችንን ከፍታ እናረጋግጣለን!" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው አውደ ርዕይ ለሶስት ቀናት ለህዝብ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ነው።

የሀዋሳ ኤስ ኦ ኤስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአፈርን ርጥበትና የሙቀት መጠንን በመለካት ለአትክልት በራሱ ጊዜ ውሃ የሚያጠጣ ግኝት በአውደ ርዕዩ ላይ ከቀረቡት የፈጠራ ስራዎች ይገኙበታል።

በአውደ ርዕዩ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ በየነ በራሶ  እንዳሉት፤ ቢሮው በሳይንስ መስክ ላይ በማተኮር የተሟላ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸው  ተማሪዎችን ለማፍራት ትኩረት ሰጥቷል።

ተማሪዎች በተግባር የተደገፈ ጥራት ያለው ትምህርት አግኝተው አዲስ ሀሳብ አፍላቂና ሀገር ተረካቢ እንዲሆኑ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

መንግስት የትምህርት ጥራት ችግር ለማረጋገጥ  የትምህርት ፍኖተ ካርታ በማውጣት ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመው፣ ይህን በመጠቀም የተሟላ ስብዕና ያለው ተማሪ ለማፍራት መምህራን በትኩረት እንዲሰሩም አሳስበዋል።

ተማሪዎች ሙሉ ትኩረታቸውን በትምህርት ላይ አድርገው በመማር ነገ ለሚረከቧት ሀገራቸው አዲስ ሀሳብ አፍላቂ ለመሆን ጥረት እንዲያደርጉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ጸጋዬ ቱኬ በበኩላቸው፤ ለሳይንስ፣ ለፈጠራ ስራና ጥራት ላለው ትምህርት ትኩረት የሰጡ ሀገራት የተሻለ ደረጃ መድረስ የቻሉት በተግባር የተደገፈ ትምህርት በመስጠታቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በስሩ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በዕውቀትና ክህሎት የተሟላ ስብዕና ያለው ተማሪ ማፍራት እንዲችሉ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታቀውዋል።

 የትምህርት ዘርፍ ባለድርሻ አካላት የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ባደረጉት ርብርብ የተገኘውን ውጤት በጥራቱ ላይም ለመድገም ድጋፍ እንዲያደርጉ የጠየቁት ደግሞ የከተማው  ትምህርት መምሪያ ሀላፊ አቶ ደስታ ዳንኤል ናቸው።

ተማሪዎች በሳይንስና ሂሳብ የትምህርት ዘርፍ ያላቸው ፍላጎትና አመለካከት በመቀየሩ የተነሳ 11ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ መስክን የሚመርጡ ተማሪዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸዋል።

በትምህርት መስክ ምርጫ ወቅት ወላጆች ልጆቻቸው ማህበራዊ ሳይንስ መስክ እንዳይገቡባቸው ጥያቄ እንደሚያቀርቡም ጠቁመዋል።

 የተፈጥሮ ሳይንስ መስክን ተመራጭና ተወዳጅ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመው የተማሪዎችን ፍላጎት ለማነሳሳት ሲባል አውደ ርዕዩ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

የሀዋሳ ኤስ ኦ ኤስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ዮናታን አማረበሰጠው አስተያየት  "ከጓደኛዬ ጋር በመሆን የሰራሁት ያለ ሰው በራሱ ሰዓት የአየር ሁኔታውንና የአፈሩን እርጥበት መጠን በመለካት ውሃ የሚያጠጣውን ግኝት የሰራነው ከትምህርት ቤቱና መምህራን ባገኘነው ድጋፍ ነው" ብሏል።

ግኝቱ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በማይኖርበት አካባቢ በጸሀይ ብርሀን መስራት እንደሚችልና በግብርናው መስክ ያለውን ጠቀሜታ በማየት ድጋፍ የሚያደርግላቸው ካገኙ አምርተው ለማቅረብ እንደሚችሉ ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም