የበካይ ጋዞች ልቀት እየጨመረ በመምጣቱ የማህበረሰብ ጤና ላይ ከፍተኛ ችግር እያስከተለ ነው

389

መጋቢት 29/2014(ኢዜአ)  የበካይ ጋዞች ልቀት እየጨመረ በመምጣቱ የማህበረሰብ ጤና ላይ ከፍተኛ ችግር እያስከተለ በመሆኑ ሁሉም በመከላከል የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ።

በመከላከል ሂደቱ በተለይም ተቋማት የአካባቢ ጥበቃን ስራን የእቅዳቸው አንድ አካል አድርገው እንዲሰሩም ተጠይቋል።

የአለም ጤና ቀን  "አለማችን የጤና አለኝታችን" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ታስቦ ውሏል፡፡

በበካይ ጋዞች ልቀት ምክንያት በሚከሰት በሽታ በአለም ላይ በየአመቱ በአማካይ 13 ሚሊዮን ሰዎች ህይወታቸውን እንደሚያጡ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

በተለይም የቤት ውስጥ የአየር ብክለት በዓለም ላይ ከምግብ እጥረት በመቀጠል ሁለተኛው የሞት መንስኤ ሲሆን 12 ነጥብ 5 በመቶ የበሽታ ስርጭት ምክንያትም ሆኗል።

እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች ለሆኑ ህጻናት ሞትም የቀዳሚውን ድርሻ በመያዙ እልባት የሚሻ የጤና ጉዳይ መሆኑ ተገልጿል።

የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ፤ በተለይም ከኢንዱስትሪዎች መስፋፋትና የበካይ ጋዞች ልቀት ጋር ተያይዞ የአካባቢ ብክለት መጠን እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል።

የአየር ብክለት መጨመር በተለይም ለልብና የመተንፈሻ አካላት ህመም እና ሌሎችም በሽታዎች መባባስ ምክንያት እየሆነ በመምጣቱ ችግሩን የመቀነስ ጉዳይ የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

የምንተነፍሰው አየር፣ የምንጠጣው ውሃ እና የምንኖርበት አካባቢ የብክለት መጠን አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንም ተናግረዋል።

ለአየር ብክለት መባባስ ምክንያት እየሆኑ ያሉ ጉዳዮችን በመለየት ሁሉም ሴክተር መስሪያቤቶች የእቅዳቸው አንድ አካል አድርገው በመከላከል ላይ አተኩረው ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት።

ችግሩን ለመቀነስ ጭስ አልባ የሃይል አማራጮችን ማስፋትና በኢነርጅ ዘርፍ የተሰሩ መልካም ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

የጤና ሚኒስትር ተቋማት ችግሩን ለመፍታት በሚያደርጉት ጥረት እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ የአለም ጤና ድርጅት ተወካይ ዶክተር ቦሪማ ሳምቦ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚመጡ በሽታዎች የሰውን ልጅ ህይወት አደጋ ላይ ጥለውታል ብለዋል፡፡

በአለም አቀፍ ደረጃ ችግሩን ለመከላከል በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው የሁሉም አካላት ተሳትፎና ትብብር ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

በዚህ ዙሪያ የኢትዮጵያ መንግስት በተለይም የአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብርን በማስፋት ለአየር ንብረት ለውጥ መስተካከል የድርሻውን በመወጣት ላይ ይገኛል ብለዋል።

የአለም ጤና ድርጅትም ይህንኑ መልካም ተሞክሮ ለማስፋት ለሚደረገው ጥረት ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም