በሴቶች የሚከናወን የከተማ ግብርና ማስጀመሪያ ስነ ስርአት እየተካሄደ ነው

119

ሶዶ፤ መጋቢት 29/2014(ኢዜአ) በሀገር አቀፍ ደረጃ በሴቶች ተሳትፎ የሚከናወን የከተማ ግብርና ማስጀመሪያ ስነ ስርአት በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ ስራ አስፈጻሚ አባላትና ሌሎች የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በወላይታ ዞን  "ምግባችን ከጓሯችን፤ ጤናችን ከምግባችን" በሚል መሪ ቃል የከተማ ግብርና ማስጀመሪያ ንቅናቄ በመካሄድ ላይ ነው።

በልማቱ ማስጀመሪያ ስነ ስርአቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ዓለሙ ስሜ፤ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት የምግብ አቅርቦትን መጨመር እንደሚቻል አመልክተዋል።

ማንኛውም ቦታ ፆሙን ማደር እንደሌለበት ያነሱት ዶክተር ዓለሙ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ የመትከልና የማልማት ስራው በትኩረት ቢሰራ ውጤት እንደሚያመጣ አመልክተው፤ "የቦታ እጥረት ለልማቱ ምክንያት ሊሆን አይገባም" ብለዋል።

በወላይታ ዞን ወርባቢቾ ቀበሌ በመስክ ጉብኙት የተመለከቱት በግለሰብ ጓሮ የለማ አትክልት የሚበረታታ መሆኑን አመልክተው፤ ስራው  ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የፓርቲው ሴቶች ሊግ ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መሰረት መስቀሌ በበኩላቸው በሴቶች የሚከናወን የከተማ ግብርና ስራ  "ምግባችን ከጓሯችን፤ ጤናችን ከምግባችን" በሚል መሪ ቃል የተጀመረ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጀመረው የጓሮ አትክልት ልማት ስራ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ6 ሚሊዮን በላይ ሴቶች  ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።

"እንደ ሀገር ፈተና የሆነውን የኑሮ ውድነት ጫና ለመቀነስ የጓሮ አትክልት ልማት ያለው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም" ያሉት ወይዘሮ መሰረት የሴቶችን ተሳትፎ በተግባር በማጠናከር ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

በልማቱ ማስጀመሪያ ስነ ስርአት ላይ  ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሊጉ አባላትና ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን በቀጣይ ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል።

በስነ ስርአቱ በወላይታ ሶዶ ከተማ፣ ወርባቢቾ ቀበሌ እንዲሁም የሶዶ ግብርና ኮሌጅ ላይ “ምግቤን ከጓሮዬ” በሚል ሃሳብ የተከናወነ የጓሮ አትክልት ልማት ያለበት ደረጃ  የመስክ ምልከታ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም