በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት የድጋፍ ጥሪ ቀረበ

72

ደሴ ፤ መጋቢት 29/2014 (ኢዜአ) በአሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት የሚደረገውን ቅንጅታዊ ጥረት ሁሉም በሚችለው እንዲደግፍ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ጥሪ አቀረቡ።

ሚኒስትሯ  በምስራቅ አማራ በሽብር ቡድኑ የወደሙ 18 ማህበራዊ ተቋማትን መልሶ የመገንባት ሥራን ዛሬ በከሚሴ ከተማ ተገኝተው አስጀምረዋል።

በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ሚኒስትሯ እንደገለጹት፤ አሽባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ሀገረን  ለማፍረስ በቅንጅት ቢሰሩም በኢትዮጵያዊያን አንድነት ሴራቸውን ማክሸፍ ተችሏል።

አሸባሪው ህወሓት በአማራ እና አፋር ክልሎች ወረራ በፈጸመበት ወቅት በንጹሀን ላይ ከፈጸመው ግድያና ግፍ በተጨማሪ በከተሞች ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱን አስታውሰዋል።

የወደሙ ተቋማትን በመገንባት መልሰው አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ መንግስት የተለያዩ አጋር አካላትንና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የተቋማቱ መልሶ ግንባታ ሥራ ከዓለም ባንክ  በተገኘ 150 ሚሊዮን ብር እንደሚከናወን ገልጸው " ሥራውን በአራት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል" ብለዋል።

ማህበራዊ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም እየተደረገ ያለውን ጥረት ሁሉም በሚችለው ድጋፍ በማድረግ እንዲያግዝም  ሚኒስትሯ  ጥሪ አቅርበዋል።

እንደሚኒስትሯ ገለጻ፣ ህብረተሰቡ ለሚነዙ ሀሰተኛ መረጃዎች ትኩረት ሳይሰጥ የኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም በዘላቂ መሰረት ላይ ለማቆም መስራት አለበት።

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ጌታቸው ጀንበር በበኩላቸው "አሸባሪው ህወሓት በክልሉ ከፍተኛ ውድመት ቢያደርስም ተቋማትን በቅንጅት መልሶ በማቋቋም በከፊልም አገልግሎት እንዲሰጡ ጥረት እየተደረገ ነው" ብለዋል።

የሽብር ቡድኑ የጤና እና የትምህርት  ጨምሮ በተለያዩ ማህበራዊ ተቋማት ላይ ዘረፋና ውድመት በማድረስ ለህዝብ ያለውን ጥላቻ በተግባር ማሳየቱን ገልጸዋል።

ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሰባት ከተሞች ተለይተው የመልሶ ግንባታ ሥራው ዛሬ መጀመሩንም አረጋግጠዋል።

የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔትና ሥራ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት  ኃላፊ አቶ መኮንን ያኢ፤  ዛሬ ግንባታቸው የተጀመሩ ተቋማት በተያዘላቸው ጊዜ በጥራት እንዲጠናቀቁ ቅንጅታዊ ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

በከሚሴ ከተማ በአሸባሪዎቹ ህወሓት እና ሸኔ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የከተማዋ አስተዳደር  ከንቲባ ወይዘሮ ከድጃ አሊ ናቸው።

ዛሬም አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትና አንድ አገልግሎት መስጫ ተቋም ለመገንባት የግንባታ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።

በመርሀ ግብሩ ላይ የፌዴራልና የክልል  ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የተገኙ ሲሆን በከሚሴ ከተማም የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም