ግብርን በአግባቡ በመክፈል ኢኮኖሚውን ልንደግፍ ይገባል -ግብር ከፋዮች

115

ሀዋሳ፤ መጋቢት 29/2014 (ኢዜአ)፡ ግብርን በአግባቡና በወቅቱ በመክፈል ኢኮኖሚውን ልንደግፍ ይገባል ሲሉ በሲዳማ ክልል ግንባር ቀደም ግብር ከፋዮች አመለከቱ፡፡

በክልሉ ባለፈው ዓመት ግንባር ቀደም ግብር ከፋይ በመሆን እውቅናና ሽልማት ከተሰጣቸው ባለሀብቶች መካከል  የአድማስ ተስፋ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ አስቻለው አድማሱ አንዱ ናቸው፡፡

ድርጅታቸው ሀዋሳን ጨምሮ በሲዳማ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች መሰማራቱን ገልጸው፤ ከዓመቱ ሞዴል ግብር ከፋዮች መካከል ቀዳሚው መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ዜጋ ግብር መክፈል የሀገር ፍቅር የሚገለጽበት አንዱ መንገድ መሆኑን ጠቅሰው፤ እውቅናና ሽልማቱ የተሻለ ለመስራት አቅም እንደሚፈጥርላቸው አመልክተዋል።

''ሀገር በውጭ ጫና ውስጥ በገባችበት በዚህ ወቅት የንግዱ ማህበረሰብ አባላት የሚጠበቅብንን ታክስና ግብር በአግባቡ በመክፈል ኢኮኖሚውን ልንታደግ ይገባል'' ብለዋል፡፡

''ነግዶ ማትረፍ የሚቻለው ሀገር ስትኖር ነው'' ያሉት ባለሀብቱ፤ በ2013 በጀት ዓመት ድርጅታቸው ከ6 ሚሊየን ብር በላይ ግብር መክፈሉን ተናግረዋል።

ሀገር እንደ ሀገር ተጠናክራ የምትቀጥለው ዜጎች የሚጠበቅባቸው ሲወጡ መሆኑን አመልክተው፤ በቀጣይም ሀገራዊ ድርሻቸውን እንደሚወጡ ጠቁመዋል።

ባለፈው ዓመት 34 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በመክፈል 1ኛ ተሸላሚ የሆነው የኢታብ ሳሙና ፋብሪካ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ አበበ በበኩላቸው ሀገር የንግዱን ማህበረሰብ ድጋፍ የምትፈልግበት ጊዜ አሁን መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኑሮ ውድነትና የአንዳንድ ምዕራባዊያን ሀጋራት ጫና ለመመከት የንግዱ ማህበረሰብ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ጠቁመው፤ ድርጅታቸው የሚጠበቅበትን ግብር በአግባቡና በወቅቱ እከፈሉ መሆኑን ተናግረዋል።

ድርጅታቸው ለተከታታይ ዓመት በግንባር ቀደም ግብር ከፋይነት የግሪን ካርድ ተሸላሚ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም የተሻለ ሰርተው ተገቢውን ግብር እንደሚከፍሉ አመልክተዋል።

ክልሉ የሰጣቸው እውቅናና ሽልማት የበለጠ ለመስራት እንደሚያነሳሳቸው የገለጹት ደግሞ በዓመቱ 7 ሚሊየን ብር በመክፈል ግምባር ቀደም ግብር ከፋይ የሆኑት የአርፋሳ ጄኔራል ትሬዲንግ ስራ አስኪያጅ አቶ ታሪኩ በኔራ ናቸው።

''ግብር መሰወር ከእናት መቀነት እንደመስረቅ ይቆጠራል'' ያሉት አቶ ታሪኩ፤ ድርጅታቸው ግልጽ የሆነ ግዥና ሽያጭ በመፈጸምና ከሚያገኘው ትርፍ ተገቢውን በመክፈል የሚጠበቅበትን እየተወጣ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ሀገር ከገባችበት ችግር የምትወጣው ኢኮኖሚዋን ማሳደግ ስትችል መሆኑን ጠቁመው፤ ''በተለያዩ ዘርፍ የተሰማራን የንግድ ማህበረሰብ አባላት ግብርና ታክስን በአግባቡ በመክፈል ድጋፍ ማድረግ ይኖርብናል'' ብለዋል፡፡

የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን ሃላፊ አቶ ሃይሉ ጉዱራ በበኩላቸው ክልሉ በበጀት ዓመቱ ሊሰበስብ ካቀደው 5.5 ቢሊየን ብር ውስጥ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 3 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡        

ባለፈው ዓመት ግብር በመክፈል ግንባር ቀደም የሆኑ ግብር ከፋዮች በዘንድሮውም ዓመት ይደግማሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸው፤ የክልሉን ገቢ ለማሳደግ የግብር ከፋዮቹ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ግብርን በጊዜ በማይከፍሉና በሚያጭበረብሩ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ጥብቅ ክትትል እንደሚደረግ አመልክተዋል።          

ክልሉ ሰሞኑን በሀዋሳ ለ2013 ዓ.ም ግንባር ቀደም ግብር ከፋዮች የእውቅናና ሽልማት ስነ ስርአት መዘጋጀቱ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም