ደመናን የማበልጸግ ቴክኖሎጂ ደመናን የሚፈጥር ሳይሆን በተከማቸ ደመና ተጨማሪ የዝናብ ውሃ ለማግኘት የሚውል ነው

102

መጋቢት 29 2014(ኢዜአ) ደመናን የማበልጸግ ቴክኖሎጂ በራሱ ደመና የሚፈጥር ሳይሆን በተከማቸ ደመና ተጨማሪ የዝናብ ውሃ ለማግኘት የሚውል መሆኑን ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

የብሔራዊሚቲዎሮሎጂኢንስቲትዩት ደመና የማበልጸግ ቴክኖሎጂን በሚመለከት ለሚነሱ የተሳሳቱ አመለካከቶች ግልጸኝነት ለመፍጠርሲልለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ማብራሪያ ሰጥቷል።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ክንፈ ኃይለማርያም፤በማብራሪያቸው ደመና የማበልጸግ ቴክኖሎጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን በኢትዮጵያም በሙከራ ደረጃ እየተተገበረ መሆኑን ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂው በዋናነት በከባቢ አየር ላይ የሚገኝ የደመና ቁልልን ከላይ በአውሮፕላን ወይም በድሮን እንዲሁም ከታች ከከፍታ ቦታ በተተከለ ጀነሬተር አማካኝነት እንደ ሶድየም ክሎራይድ ያሉ ጨዋማ ኬሚካሎችን በመርጨት ወደ ዝናብ የሚቀይር መሆኑን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያም በአውሮፕላንና ከከፍታ ቦታ በተተከሉ ጀነሬተሮች አማካኝነት ሶዲዬም ክሎራይድ (የገበታ ጨው) ወደ ደመና በማድረስ ቴክኖሎጂው እየተተገበረ መሆኑን አስረድተው"ቴክኖሎጂው በራሱ ደመና ፈጥሮ ዝናብ እንደሚያዝነብ በማስመሰል በአንዳንዶች የሚጠቀሰው አገላለጽ የተሳሳተ አረዳድ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂው የታጠበ ልብስን ወይም እርጥብ ስፖንጅን ደጋግሞ የመጭመቅ ያህል ቁልል ደመናዎች ተጨማሪ ዝናብ እንዲሰጡ የሚያደርግ እንጂ ደመና በሌለበት ደመና ፈጥሮ ዝናብ የሚያዘንብ አለመሆኑን አብራርተዋል፡፡

ቴክኖሎጂው ጥቅም ላይ እንዲውል ደግሞ በከባቢ አየር ላይ ቁልል ደመና ሊኖር እንደሚገባ ጠቅሰው በዚህም በተከማቸ ደመና አማካኝነት ተጨማሪ የዝናብ ውሃ ለማግኘት ይውላል ነው ያሉት፡፡

በመሆኑም አብዛኛውን ጊዜ የተራዘመ ድርቅ በሚከሰትባቸው አካባቢዎች ዝናብ መፍጠር የሚያስችል ደመና ስለማይኖር ቴክኖሎጂውን ብቸኛ የድርቅ መፍትሄ አድርጎ መውሰድ እንደማይገባ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ እየተከናወነ ባለው ደመና የማበልጸግ የሙከራ ትግበራም ከፍተኛ  የእውቀት ሽግግር ማድረግ ተችሏል ያሉትሃላፊው ከመረጃ መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር በመተባበር ከመሬት ወደ ደመና ኬሚካል የሚረጭ ጀነሬተር እንዲሁም  ደመና ለማበልጸግ የሚረዳ ኬሚካል በአገር ውስጥ ማምረት መቻሉን ለአብነት አንስተዋል፡፡

በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል የማፍራት እንቅስቃሴ እየተከናወነ መሆኑንና አሁን ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ የአየር ሁኔታ ለመከታተል የሚያስችል አንድ ራዳር ብቻ መኖሩን ጠቅሰዋል።

በተያዘው ዓመት በተለያዩ አካባቢዎች ተጨማሪ ሶስት ራዳሮችን በመትከል ቴክኖሎጂውን ይበልጥ ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚሰራም ገልጸው በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳር ቁጥር 12 ለማድረስ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

የደመና ማበልጸግ ቴክኖሎጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ በበርካታ አገራት ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን ቻይና የ2008 ቤጂንግ ኦሊምፒክ መክፈቻ እና መዝጊያ መርሐግብር  ከመጀመሩ ቀደም ብላ  በቴክኖሎጂው አማካኝነት ዝናብ በማዝነብ መርሐግብሩ እንዳይሰተጓጎል ማድረግ መቻሏ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም