ህሊና ከምንም በላይ ነው …

229
በሰውነት ጀምበሩ (ኢዜአ) የሰው ልጅ “ህሊና” ከፍትህና ነፃነት ጋር የጠበቀ ተያያዥነት  አለው፡፡ ፍትህ እና ነጻነትም ስለ  እኩልነት መረጋገጥን ያወሳሉ። የአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን ፈላስፋ ቶማስ ሆብስ እንደሚለው “ሰዎች እኩልነታቸው ያለው በተፈጥሯቸው ላይ ነው፡፡ በተፈጥሯቸው ደግሞ ጨካኝና መሰሪ ናቸው፡፡ እኩል የሚያደርጋቸው ይኼ ባህሪያቸው ግን ህይወታቸውን በክፋትና አደጋ የተሞላና አጭር ያደርገዋል …”፡፡ ስለዚህ ግለሰቡ ህሊና ቢኖረው እንኳን… ከራሱ ህሊና ጋር የተጣላ መሆኑ የማይቀር ይሆናል፡፡ ግጭቱ በሰውኛ ህሊናው እና በተፈጥሮ ፍትሀዊነት መሀል የሚደረግ እንደሆነ ሁሉ ጠንቅቆ ሳይረዳ ይታወካል፡፡ ግለሰቡ የራሱን ህሊና ከማህበረሰቡ ጋር ለማስታረቅ ደግሞ ሌላ እንቅፋት  ነው፡፡ የ18ኛው ክፍለ ዘመን የእንግሊዙ ፈላስፋ ጆን እስቲዋርት ሚል  በማህበረሰብ ህሊና (ባህል/አመለካከት) የግለሰብ ህሊና ላይ የሚደርሰውን ጭቆና ‹‹the tyranny of the majority›› ሲል ይጠራዋል፡፡ የማህበረሰቡን ጭቆና በግለሰብ አቅሙ ስለማይችለው፣ የግለሰብ ህሊናውን ለማህበረሰቡ ይሸጣል፡፡ አልያም ከማህበረሰቡ የበለጠ ሀያል ሆኖ በማህበረሰቡ ላይ ስልጣን ለመቆናጠጥ ይጥራል፡፡ ጥረቱን ለማሳካት የሚያደርገው ሙከራ በጥበብ ወይንም በፍልስፍና መልክም ሊገለፅ ይችላል፡፡ የጀርመኑ ፈላስፋ  ፍሬድሪክ ኒቼ  እንደሚለው ከማህበረሰቡ ውል ለማፈንገጥ ሲል የአራዊትን የጉልበተኝነት ህግ ለሰዎች ምርጥነት ማስረጃ አድርጎ መስበክም የዚሁ ግጭት መገለጫ ይሆናል፡፡ በመሆኑም እኩልነትን እውን ማድረግ አስቸጋሪ የፅንሰ ሀሳብ መሰረት ያለው ጥያቄ ነው፡፡ ለምሳሌ ‹‹ዴሞክራሲ›› የሚለው ፅንሰ ሀሳብ በሰዎች ዘንድ እኩልነትን ነው ወይንስ ነፃነትን ለመስጠት ነው የሚያገለግለው?  ነፃነት (Freedom) እና አርነት (liberty) በሚሉት ቃላት መሀል እንኳን እኩልነት የለም፡፡ አርነት ከአንዳች የገዢ ጭቆና መውጣትን የሚያመለክት ቃል ነው። ነፃነት ግን በሁለት ዘውግ የተከፈለ ሀሳብ ነው፡፡ አዎንታዊ ነፃነት (Positive freedom) ማለት ሰዎች ለህልውናቸው ምክንያት የሆነ አንዳች የሕይወት ግብን ተከትለው ወደ አለሙበት ለመድረስ ምርጫቸውን መሰረት አድርገው የሚጓዙት ጉዞ ነው፡፡ ወደዚህ ግብ ከመድረስ የሚያግዳቸው ሁሉ ይኸንን አዎንታዊ ነፃነትና የህይወት ትርጉማቸውን የሚያሰናክል ጨቋኛቸው ነው፡፡ ሌላው የነጻነት አይነት ደግሞ አሉታዊ ነፃነት (Negative freedom) ነው፡፡ አሉታዊው ነፃነት ማንም ሰው ያሰኘውን ፍላጎቱን ያለ ምንም ቅድመ ምክንያታዊነት ለመፈፀም የሚያስችለው የነፃነት አይነት ነው፡፡ ለምሳሌ፤ አንድ ሰው የመቃም ወይንም የማጨስ ነፃነቱን ሲጠቀም ምርጫው አካሉን ወይንም የህይወት ዘመኑን ሊያሳጥር እንደሚችል አውቆ ነው፡ ግን እያወቀም… ከራሱም ህሊና ወይንም ከማህበረሰቡ አሊያም ከህግ የበለጠ የፍላጎቱን ነፃነት ለመጨበጥ ሲል ምርጫውን ተግባራዊ ያደርጋል ማለት ነው፡፡ እነዚህ ሁለት የነፃነት አይነቶች … ራሳቸው በአንድ ግለሰብ ውስጥ ሳይስማሙ.. ወይንም እኩል ሳይሆኑ ሊቀጥሉ ይችላሉ፡፡  ለሁለት የተለያዩ የነፃነት አይነቶች… የተገዛ ሁለት አይነት ህሊና በግለሰቡ ስነልቦና ውስጥ ፈጥረው እኩልነትን ለማግኘት ሊሻኮቱ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም ህይወታቸው ዘለግ ያለ ጊዜ እንዲቆይና ትርጉም ያለው እንዲሆን ለአንድ የተመረጠ አንድ አድራጊ ንጉስ፣ እኩልነታቸውን ያስተዳድርላቸው ዘንድ ነፃነታቸውን አሳልፈው መስጠት ይኖርባቸዋል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም የፍትህ መጓደል ወይንም የነፃነት እጦት ከእኩልነት እጦት ይመነጫል፡፡ ይሄንን የማስተካከል ስራ የሚሰራ አካል፣ በግለሰቡ ልቦናም ሆነ በማህበረሰብ ልቦና ውስጥ አለ፡፡ ነገር ግን ይህንን የውስጣችንን ህሊና እና በጎ ተግባር አውጥተን ለመጠቀም የተለያዩ ምክንያቶችን እንዘረዝራለን። ለዚህ ማሳያው ለሶስት አመታት በአገራችን በተደረገው የነጻነት ና እኩልነት   ጥያቄ አሁን ላይ በተሻለ መንገድና ሁኔታ ነጻነት መከበር ተጀምሯል ማለት ይቻላል  ። ነገር ግን ይህን ነጻነት የምናይበት ጊዜና የምንተገብርበት ሁኔታ ከቦታ ቦታ የተለያየ ከመሆኑም በላይ በጅምላ የሚወሰድ ፍትህና ዕርምጃ ፣ከህሊና በላይ የሆነ የጥፋት ድርጊት ሲፈፀም ይስተዋላል። በምክንያታዊነት የሚመራ ማንኛውም ህዝብ የሚያከናውናቸው ማናቸውም ተግባሮች የበሰለ እና የሰከነ ምልከታውን ያሳያል። ህዝቡ በምክንያታዊነት ካልተመራ የማገናዘብ አቅሙን በግለሰቦች አልያም በቡድኖች በቀላሉ ሊቀማ ይችላል። ይህ ደግሞ በአንድም ይሁን በሌላ የህግ የበላይነትእንዲናድ ምክንያት በመሆን  ህግና ስርዓት እንዲደፈጠጥ ያደርጋል። ምክንያታዊነት ሲጎለብት ለህገ የበላይነት የሚኖረው ጠቀሜታ አይታበይም። ሀገራችን ተግባራዊ እያደረገች ለምትገኘው ህገ መንግስታዊ ስርዓት መጎልበትም የላቀ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ህገ መንግሰቱ የበላይ ሆኖ እስከተከበረ ድረስ በሀገራችን ውስጥ እየጎለበተ የሚሄደው ይህ ስርዓት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እያስቻለ ይመጣል። በሌላ በኩል ለግብረ ገብነት የሰው ልጅ የተሰጠውን ወይም ያለውም ህሊና እንደየብቃቱና ፍላጎቱ ስራ ላይ ያውለዋል። ህሊና በግለሰብ መስተጋብር ወይንም ነፍስ ውስጥ እኩል አድርጎ የመመዘንና ፍርድ የመስጠት ስራን ይሰራል፡፡ በግለሰቡ ውስጥ በተናጠል ህሊና ከሌለ በማህበረሰቡ ወይንም ህዝብ ውስጥ ብቻውን ተነጥሎ ሊኖር አይችልም። በግለሰብ የአካልና የአእምሮ እንዲሁም የስሜት ጥምረት ውስጥ እኩል አድርጎ የሚያስተዳድር መንግስት ከሌለ ግለሰቡ የቀውስ ዳርቻ እንደሚሆነው፣ የማህበረሰብ ህሊናም ከሌለ ውጤቱ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሁሉም ዜጋ በአንድ ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ ግንዛቤ ሊይዝ አይችልም። አብዛኛው ዜጋ ግን ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ዋልታ መሆኑን ግንዛቤ መጨበጥ ችሏል። ለዚህም ሁነኛ አስረጂ ሆኖ ሊጠቀስ የሚችለው በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ህዝቡ ህገ መንግስትን ከማክበር ባሻገር፤ ህገ መንግስቱ በሌሎች እንዲከበር  የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል። በኢፌዴሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ ዘጠኝ  ስለ ህግ የበላይነት እንደተመለከተው፤ “ህገ መንግስቱ የህጎች ሁሉ የበላይ ነው፤ ማንኛውም ህግ፣ ልማዳዊ አሰራር እንዲሁም የመንግስት አካል ወይም ባለስልጣን ውሳኔ ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም” ይላል። ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግስት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማህበራት እንዲሁም ባለስልጣኖቻቸው ህገ መንግስቱን የማክበርና ለህገ መንግስቱ ተገዥ የመሆን ሀላፊነት አለባቸው። በዚህ ህገ መንግስት ከተደነገገው ውጭ በማንኛውም አኳኋን የመንግስት ስልጣን መያዝ የተከለከለ ነው። የህግ የበላይነት በሌለበት ሀገር ማንኛውም ሰው በሰላም ወጥቶ ሊገባ አይችልም። መብት ሰጪዎችና ነሺዎች ጉልበተኞች ይሆኑና ስርዓት አልበኝነት ይነግሳል። ጉልበተኞቹም ሌሎች ዜጎችን እንዳሻቸው በማድረግ የባሪያ እና የሎሌ ስርዓት ይፈጥራሉ። ስርዓት አልበኝነት ሲነግስም ህግን አክብሮ የሚንቀሳቀስ ዜጋ አይኖርም። ሁሉም በየፊናው እየሮጠ የራሱን የበላይነት ለማስጠበቅ ይጥራል። ይህ ሁኔታም አንድን ሀገር የነበረበትን ሰላማዊ ምህዳር በማወክ በሁከት እንዲታመስ ያደርገዋል። በሰላም ውስጥ ኖሮ ሀገርን ማበልጸግና ወደ ተሻለ ህይወት መሻገር  ያበቃለታል ማለት ነው። እናም ይህን ሁኔታ ለመከላከል፣ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የህግ የበላይነት መኖር ግድ ይላል። የህግ የበላይነት መከበር ለሀገር ሰላምና መረጋጋት ብሎም ልማትን ለማሳለጥ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል። ሰላም ከጠፋ ደግሞ ስለ ልማትና ዴሞክራሲ ማሰብ አይቻልም። ፀረ ልማታዊነትና ፀረ ዲሞክራሲያዊነት ቦታውን ይረከባሉ። ሀገራችን ጥሩ የሰላም ስትንፋሷ በተስተካከለበት በዚህ ሰዓት ደግሞ የህግ የበላይነት መከበሩ ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው። በመሆኑም ሀገራችን እንደ ሀገር ፈጣን ልማትን ማምጣትና ከተመፅዋችነት መላቀቅ ብሎም ዴሞክራሲን መገንባት የሞት ሽረት ያህል የህልውናዋ ጉዳይ አድርጋ ስለያዘችው የዕድገትና ዴሞክራሲ ስርዓት ባህል ግንባታ ሂደቱ ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል፤ አሁን በዕጃችን ያለውን አንጻራዊ ነጻነትና  ሰላም የሰፈነበትን ምህዳር ጠብቆ መያዝ አስፈላጊም ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ነው። የአማራ ክልል ርዕሰ መስድተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በባህርዳር “ህዝባዊ ወገንተኝነታችንን ጠብቀን ለክልሉ ሰላም መረጋገጥ እንተጋለን” በሚል  መሪ ሃሳብ በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን እና ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን መኮንኖች የለውጥ አመራር በተዘጋጀ ስልጠና ላይ  ተገኝተው እንዳሉት ‹‹ ነጻነት ከህግ የበላይነት ውጭ ሊረጋገጥ አይችልም ››። ይህ የመጣው የሰላም፣ የፍትህ እና የፍቅር ለውጥ ህዝቡ በከፈለው ከፍተኛ መስዋዕትነት እንደሆነ የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳደሩ በተለይ ደግሞ ህዝቡ በተጎናጸፋቸው ነጻነትና ተስፋ  ማህበረሰቡ ነቅቶ መጠበቅ አለበት ነው ያሉት። ምንም እንኳ ነጻነት የመጣ ቢሆንም አንዳንድ ተግዳሮቶች እየገጠሙን ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ይህ ደግሞ ነጻነትን ተገን አድርጎ ህገ-ወጥ የሆኑ ተግባራትን የመፈጸም ስርአ - አልበኝነት አለ ብለዋል፡፡ ‹‹ነጻነትን ለብሰን የሚመጣውን ውንብድና በተቀናጀ መልኩ ካለተከላከልን ህብረተሰቡ በትግሉ ያመጣው ነጻነት ይቀለበሳል” ነው ያሉት፡ ‹‹ነጻነት ከህግ የበላይነት ውጭ ሊረጋገጥ አይችልም፡፡ የነጻነት ሌላኛው ግልባጭ ህግ አክባሪነት ማለት ነው፡፡ ህግ ከተጣሰ ነጻነት ይገረሰሳል፡፡ የነጻነት ጸሩ አምባገነንነት ብቻ ሳይሆን ስርአተ- አልበኝነት ጭምር ነው፡፡›› ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ከሶማሌ ክልል ከተውጣጡ ማህበረሰብ ጋር ባደረጉት ውይይት፤ የሕግ የበላይነትና በሕግ መግዛት ለየብቻ ነው ሲሉ፣ “የሕግ የበላይነት ማለት መንግስትም ሕዝብም በጋራ የሚያውቁትና ማንም ሊተላለፈው የማይችል እንጂ ሕግ እያወጣህ የአንተን ፍላጎት ማስረጽና ሌላውን ማፈን እንዳይሆን ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፤ እንደዚያ ካልሆነ ዴሞክራሲ በተሟላ መንገድ በአገራችን እንዲሰፋ፣ እንዲያብብ ማድረግ አይቻልም፣ የሕግ የበላይነት ጉዳይም ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም” በማለትም አብራርተዋል። የሕግ የበላይነት ከሌለ ሕገ-ወጥነት ይሰፍናል፡፡ ሕገወጥነት የበላይነቱን ሲይዝ ዜጎች በሰላም ወጥቶ የመግባትና የመኖር መብታቸው ለአደጋ ከመጋለጡም በላይ፣ ሥርዓተ አልበኝነት ሰፍኖ አገር ከማትወጣበት አደጋ ውስጥ ትገባለች፡፡ ማንም ሰው በሰላም የመኖር፣ የመሥራት፣ የመማር፣ የመንቀሳቀስ፣ ሀብት የማፍራት፣ የመሰለውን አመለካከት የማራመድና የመሳሰሉት መብቶች የሚከበሩለት የሕግ የበላይነት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ ደግሞ ተቋማት ያስፈልጋሉ፡፡ ከእነዚህ ተቋማት አንዱ ፍርድ-ቤት ሲሆን፤ ከፍርድ-ቤት ጋር ደግሞ አቃቤ ህግ፣ ፖሊስ፣ ማረሚያ ቤት፣ ጠበቆች እንዲሁም ሚዲያ መኖር አለባቸው፡፡ ፍርድ-ቤት በህገ መንግስቱ የተደነገገ ነፃነት አለው፡፡ የአፍሪካውያን የጋራ መሰባሰቢያ መሆን የቻለችው ኢትዮጵያ ሕገወጦች በሚቀሰቅሱዋቸው ግጭቶች ስትተራመስ ማየት ያማል፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድን በበላይነት መምራት ሲገባት በየሥርቻው በሚነሱ ግጭቶች ማመስ እንቆቅልሽ ነው፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ታላቅ አገር አካባቢውን አስተባብራ የሰላም ቀጣና የማድረግ ዕምቅ አቅም እያላት፣ ወደ ክፍልፋይነት ለመለወጥ የሚሹ በታታኝ ሐሳቦችን መስማትም ያስከፋል፡፡ አገር በኩርፊያ፣ በጥላቻ፣ በቂምና በቀል ትጠፋለች እንጂ መቀጠል አትችልም፡፡ የዘመናት ጠባሳዎችን በማከክ እያደሙ ሥልጣን ከሚያስገኘው ጥቅማ ጥቅም በላይ የሆነች ታላቅ አገር ግዙፍ ምሥል እያንቋሸሹ መቀጠልም ለማንም አይበጅም፡፡ ኢትዮጵያ ከተተበተበችበት ድህነትና ኋላቀርነት ብቻ ሳይሆን፣ እኔ ብቻ ነኝ የማውቅልህ ከሚባለው ጎታችና አጥፊ ጀብደኝነት መላቀቅ ይኖርባታል፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ ኋላቀርነት መላቀቅ የሚቻለው ደግሞ ከምንም ነገር በላይ ለሕግ የበላይነት መገዛት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በእኩልነት የሚኖርበት ሥርዓት ይፈልጋል። ማንም እየተነሳ የማያንገላታው፣ የማያፈናቅለው፣ የማይገድለውና ንብረቱን የማይዘርፈው በሕግ የበላይነት ሥርዓት ሲሰፍን ነው፡፡ ይህ ሥርዓት ዕውን ይሆን ዘንድ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ከተመልካችነት ወደ ተሳታፊነት መሸጋገር አለባቸው፡፡ የገዛ አገራቸውን ጉዳይ በሠለጠነና በዴሞክራሲያዊ መንገድ መነጋገር፣ መከራከርና መደራደር አለባቸው፡፡ መነጋገርና መደማመጥ የሰፈነባት ዴሞክራሲያዊት አገር የሚገነባው ሕዝብ በአገሩ ጉዳይ ቀጥተኛ ተሳታፊ ሲሆን ነው፡፡ አኩራፊነትና ሴረኝነት አገርን ያተራምሳሉ፣ ሕዝብን ለሰብዓዊ ቀውስ ይዳርጋሉ፡፡ ሕገወጦች ኩርፊያና ሴራን ስለሚፈልጉ የተሳሳተ መረጃ እየለቀቁ ሕዝብ ያባላሉ፡፡ ነውጥና ግጭት በቀላሉ የሚቀሰቀሱት ስሜታዊነት ሲበዛ ስለሆነ፣ ለምክንያታዊ አስተሳሰቦች ልዩ ትኩረት ይሰጥ፡፡ ሐሰተኛ መረጃዎች በማራገብ የተጠመዱ ወገኖችም ልብ ይግዙ፡፡ ታላላቆች ታናናሾችን፣ አረጋውያን ጎልማሶችን፣ ጎልማሶች ደግሞ ወጣቶችን ቀናውን ጎዳና ያመላክቱ፡፡ ሕጋዊነት በሕገወጥነት ላይ የበላይነት ያግኝ፡፡ ኢትዮጵያዊያን በገዛ አገራቸው በነፃነት ይኑሩ፡፡ ለአገር የሚበጀው የሕግ የበላይነት የማክበርና   ከስርዓቱም በላይ ሁሉም ዜጋ በሰብዓዊ ህሊናው ሲመራ ነውና ሁሉም ዜጋ ለሰላሙ ዘብ ይቁም መልዕክታችን ነው!      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም