በኢትዮጵያ ለሚያጋጥሙ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ከተቋማዊ ሪፎርም ባሻገር የአስተሳሰብና የአሰራር ለውጥ ያስፈልጋል

86

አዲስ አበባ መጋቢት 26/2014(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ለሚያጋጥሙ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ከተቋማዊ ሪፎርም ባሻገር የአስተሳሰብና የአሰራር ለውጥ የሚያስፈልግ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ገለጸ።

በኢትዮጵያ ያለውን አቅም በሁለንተናዊ መስኮች ተግባር ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ነመራ ገበየሁ፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ኢትዮጵያ በየዘመኑ ተቋማዊ ሪፎርሞችን ብታደርግም ስኬታማ መሆን አልቻለችም።

የውስጥና የውጭ ችግሮችን ለመሻገር ጠንካራ ተቋማት አለመኖራቸው አንዱ ምክንያት ቢሆንም የአስተሳሰብና የአሰራር ለውጥ አለመኖር ደግሞ ሌላኛው ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ ከዚህ ቀደም የኤዥያ አገራት አጋጥሟቸው የነበረ ችግር አይነት ነው ሲሉም ያብራራሉ።

ሆኖም አገራቱ ያጋጠማቸውን ችግሮች ለመሻገር ፖሊሲዎቻቸው የተቋም አደረጃጀታቸውና የፖለቲካል ኢኮኖሚ ስርዓታቸው የራሱ ድርሻ ነበረው ብለዋል።

በዓለም ኢኮኖሚ ተወዳዳሪ ለመሆን ካበቋቸው ጉዳዮች ዋነኛው ህዝባዊ የአሰራርና የአስተሳሰብ የባህል ሽግግር በማካሄዳቸው መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያም በዚሁ መንገድ መጓዝ ይጠበቅባታል ነው ያሉ።

ኢትዮጵያም ላለፉት ዓመታት ያጋጠሟትን እና አሁን ያሉ ችግሮችን ለመሻገር ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች ብለዋል ዶክተር ነመራ።

አገራዊ ችግሮችን ወደ ውጭ ከመግፋት ይልቅ ወደ ውስጥ በመመልከት በዘለቄታው ለመፍታት ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሽግግር ከባህል ሽግግር ጋር አጣምሮ እንዲጓዝና ጠንካራ ብሄራዊ ስርዓት የመገንባት ስራ መታቀዱን ገልጸዋል።

የፖለቲካል ኢኮኖሚ ምህዳሩን ጠንካራ በማድረግ ኢትዮጵያ ያቀደችው እድገትና ብልጽግና እንዲሳካ ሁለንተናዊ ጥረት ይደረጋልም ነው ያሉት።

ከዓለም የኢኮኖሚ አውድ አኳያ ኢትዮጵያ ያለችበትን ደረጃ በመገምገም ከንግድ ጋር በተያያዘ ሊመጡ የሚችሉ ጫናዎችን የመቋቋሚያ መንገዶችን መንግስት በማጤን ላይ ነው ብለዋል።

በዚህም መንግስት ተቋማዊ ሪፎርሞችና የፖሊሲ ማስተካከያዎችን በማካሄድ በቀጣይ ችግሮችን ተሻግሮ ወደ ስኬት ለመድረስ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከቴክኖሎጂና ከአኗኗር ባህል ጋር የተገናኙ ለውጦችን በአግባቡ ለማስተናገድና እኩል ለመራመድ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን በትኩረት ማጤን እንደሚገባ መንግስት ትኩረት ሰጥቶታል ነው ያሉት።

ከዘመናዊው ዓለም ጋር ኢትዮጵያን ወደ ፊት ሊያሻግር የሚችል የባህል ሽግግር መካሄድ እንደሚገባ በመንግስት ታምኖበት እየተሰራ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

በተለይም ያለውን ማህበራዊ እምቅ ሀብት በተጠና ሁኔታ ጥቅም ላይ ለማዋል መታቀዱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ይምትችልበት አቅሙ ቢኖራትም የምርትና የአመጋገብ ስርዓቱ ችግሮች እንዳሉበት ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በቀጣይ ከአመጋገብ፣ ከባህልና ከአኗኗር ጋር የተያያዙ የአስተሳሰብና የሰራር ስርዓቶችን በመገምገም መቀጠል ያለባቸውና ሊቀየሩ የሚገቡ ጉዳዮችን በመለየት ወደ ፊት የመቀጠል እቅድ መያዙን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ እድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች የሆኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶች ቢኖሩም ባለው የስራ ባህል ደካማነት ለአገር እድገትና ልማት ተሳትፏቸው ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይም የሰራተኛ ምርታማ አለመሆን ከክፍያ እና ከኢንዱስትሪ ባህል ጋር ብቻ የተያያዘ ባለመሆኑ የትምህርት ስርዓቱ ላይና የአስተሳሰብ ጉዳይ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም