የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለአገልግሎት ማብቃት ቀዳሚ ሥራ ሊሆን ይገባል-- አቶ ርስቱ ይርዳው

73

ሀዋሳ መጋቢት 25/2014(ኢዜአ) በደቡብ ክልል የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በማጠናቀቅ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ የወቅቱ ቀዳሚ ሥራ ሊሆን ይገባል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው አስገነዘቡ።

በርዕሰ መስተዳድሩ የተመራ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ቡድን በስልጤ ዞን በክልሉና በፌዴራል መንግስት እየተከናወኑ ያሉ የመንገድ፣ የመጠጥ ውሀና የመስኖ ግንባታ ሥራዎችን ተመልክቷል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው በወቅቱ እንዳሉት የህዝቡን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ጥያቄ ለመመለስ በክልሉ ከ100 በላይ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ግንባታ በመከናወን ላይ ናቸው።

"ከፕሮጀክቶቹ መካከል 21ዱ ግንባታቸው በተያዘው በጀት ዓመት ተጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት በልዩ ትኩረት እየተሰራ ይገኛል" ብለዋል።

ብልጽግና ፓርቲ በቅርቡ  ባካሄደው ጉባኤ ከተቀመጡ አቅጣጫዎች የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ፈጥኖ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ማብቃት አንዱና ዋነኛ መሆኑን ገልጸው ከፓርቲው ጉባኤ በኋላ ከህዝብ ጋር በተደረገ ውይይት የልማት ፕሮጀክቶች መጓተት ህዝቡ ለኑሮው እንቅፋት እንደሆነበት ማንሳቱን አመልክተዋል።

በዚህም በግንባታ መጓተት ምክንያት ከህዘብ የተነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ነው ርእሰ መስተዳድሩ የገለጹት።

የክልሉ ውሃ፣ ማእድንና ኢነርጂ ቢሮ ሀላፊ አቶ አክሊሉ አዳኝ በበኩላቸው፣ በክልሉ ያለውን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋን ለማሳደግ በሁሉም አካባቢዎች በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ከግንባታዎቹ ውስጥ የወራቤ ከተማ የመጠጥ ውሃ ማስፋፊያ፣ የላንፍሮ፣ የስልጤ፣ የዳሎቻ፣ የአንጀሌና ዳሎቻ የመጠጥ ውሀ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የደቡብ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር አበባየሁ ታደሰ በበኩላቸው በክልሉ በራስ አቅምና በፌዴራል መንግስት ድጋፍ ከ1 ሺህ በላይ የተለያዩ የመንገድ ግንባታዎች እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል።

በገጠር ቀበሌ ተደራሽ መንገድ ልማት ፕሮጀክት እንዲሁም በክልሉ መንገዶች ባለስልጣን እየተከናወኑ ካሉ የተለያዩ የመንገድ ሥራዎች ውስጥ 500 ኪሎ ሜትር የሚሆነውን አጠናቆ በተያዘው በጀት ዓመት ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በግብርናው ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማምጣት በተያዘው አቅጣጫ መሰረት  በክልሉ የመስኖ ግንባታ በተከናወነባቸው በሁሉም አካባቢዎች የመንገድ ግንባታ ሥራዎች እየተካሄዱ መሆኑን ገልጸዋል።

"አርሶ አደሩ የሚያመርተውን ምርት በቀላሉ ለገበያ ማቅረብ እንዲችል የመንገድ ሥራውን ከመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ጋር በማስተሳሰር እየተከናወነ ነው" ሲሉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም