በቃሊቲ ኢንዱስትሪ መንደር ኤሊያስ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ 350 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወደመ

211

መጋቢት 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) ቃሊቲ ኢንዱስትሪ መንደር በኤሊያስ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ 350 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ላይ ውድመት መድረሱ ተገለጸ።

የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ትናንት ምሽት 3:15 ሰአት ላይ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታዉ ቃሊቲ ኢንዱስትሪ መንደር በኤሊያስ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ላይ የእሳት አደጋ ደርሷል።

“ከባለንብረቶቹ በደረሰን መረጃ መሰረት 350 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት ላይ ወድመት ደርሷል” ብለዋል።

በፋብሪካዉ ያሉት የጨርቅ ማቅለሚያ ኬሚካሎችና በመጋዘን ዉስጥ የሚገኙ ጥሬ እቃዎች እሳቱ ፈጥኖ እንዲስፋፋ ከማድረጋቸዉም በላይ በፋብሪካዉ ቅጥር ግቢ ዉስጥ ለመግባት አመቺ አለመሆኑ እንዲሁም ፋብሪካዉ ህንጻ ላይ መሆኑ እሳቱን በቀላሉ መቆጣጠር እንዳይቻል አድርጎታል ብለዋል።

በተከናወነው የአደጋ መቆጣጠር ርብርብ ከሌሊቱ 7 ሰዓት እሳቱን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር መቻሉን ገልጸዋል።

የእሳት አደጋውን ለመቆጣጠር 15 የእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎች 6 ውሃ የጫኑ ቦቴዎች እንዲሁም 154 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ተሰማርተዋል፤ እሳቱን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋትም 500 ሺህ ሊትር ውሃና 7 ሺህ 800 ሊትር ኬሚካል ፎም ጥቅም ላይ ውሏልም ብለዋል።

May be an image of outdoors

የእሳት አደጋዉ በአካባቢዉ ባሉ ሌሎች ፋብሪካዎች ተዛምቶ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ከፍተኛ ርብርብ ተደርጓል በዚህ ሂደትም 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የተገመተ ንብረት ማዳን መቻሉን ገልጸዋል።

አቶ ንጋቱ እንዳሉት፤ በአደጋ መቆጣጠሩ ሂደት የአየር መንገድና የደብረዘይት እሳት አደጋ ባለሙያዎች እንዲሁም የፌዴራል ፖሊስ የአዲስ አበባ መንገዶችና ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን 6 የውሃ ቦቴ በማቅረብ ተባብረዋል።

በሌላ በኩልም የጸጥታ አካላት አስፈላጊዉን ትብብር ማድረጋቸውን ገልጸው፤ በስራ ላይ በነበሩ ሦስት የፋብሪካዉ ሰራተኞች ላይ ቀላል ጉዳት የደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የስራ ኢንተርኘራይዝና ኢንደስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዣንጥራር አባይ ቦታዉ ድረስ በመገኘት በአደጋ ጉዳት የደረሰባቸዉን ባለንብረቶችን ማጽናናታቸውም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም