የጎንደር ከተማን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ክልሉ ያግዛል- ዶክተር ይልቃል ከፋለ

271

ጎንደር ፤ መጋቢት 24/2014 (ኢዜአ) የጎንደር ከተማን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት በማገዝ በኩል የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ተናገሩ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ የአንገረብ የመጠጥ ውሃ ግድብን  ከደለል የማጽዳት ስራ ዛሬ ማምሻውን ተመልከተዋል፡፡

በዚህ ወቅት  እንዳሉት፤ በከተማው በፍጥነት እየጨመረ ከመጣው  ነዋሪ ህዝብ አንጻር የንጹህ መጠጥ ውሃ  አቅርቦት በበቂ መጠን ማዳረስ አልተቻለም፡፡

የከተማውን  የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት ከመፍታት አንጻር የመገጭ የመስኖና የመጠጥ ውሃ ግድብ ግንባታ እንዲፋጠን ጥረት እንደሚደረግ ገልጸው፤  ሌሎች አማራጮችን ማመቻቸት ጊዜ የሚሰጠው አደለም ብለዋል፡፡

ለረጅም ዓመታት አገልግሎተ የሰጠውን የአንገረብ የመጠጥ ውሃ ግድብ በደለል  የመሞላት ችግር በመፍታት  በቴክኖሎጂ  ታግዞ  ውሃ የመያዝ አቅሙን ለማሳደግ የተጀመረውን ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ደለል የማውጣቱን ጅምር ያበረታቱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የከተማው የመጠጥ ውሃ ችግር ለማቃለል እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡

ባለፉት 8 ወራት ከ700ሺ ሜትር ኪዩብ በላይ ደለል ከግድቡ ማውጣት ተችሏ ያሉት ደግሞ የከተማው ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ  መኳንንት ቢራራ ናቸው፡፡

ከ4 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የደለል አፈር ግድቡ ውስጥ መግባቱን ጠቁመው፤ ዘንድሮ  1ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ  ለማውጣት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በደለል ምክንያት የግድቡ ውሃ የመያዝ አቅሙ ከ5 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ወደ 2 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ዝቅ ማለቱን ጠቅሰዋል፡፡

የአንገረብ ግድብ ለከተማው በቀን ከሚሰራጨው የንጹህ መጠጥ ውሃ ውስጥ 62 በመቶውን እንደሚሸፍን ጠቁመው፤ 10ሺ ሜትር ኪዩብ የመጠጥ ውሃ ከግድቡ በቀን በማጣራት ለህዝቡ እየተሰራጨ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት  በአንድ የውጪ ሀገር ኩባንያ የደለል ማውጣት ስራው እየተካሄደ እንደሚገኝ ተመለክቷል፡፡

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችንና  የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ የደለል የማጽዳት ስራ  ተመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም