51ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር በመከላከያ አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

205

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 24/2014(ኢዜአ) ለስድስት ተከታታይ ቀናት በሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ሲካሄድ የቆዬው 51ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር በመከላከያ ስፖርት ክለብ አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቀቀ።

ከመጋቢት 19 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ የተካሄደው የአትሌቲክስ ሻምፒዮናው ውድድር ፍፃሜውን ዛሬ አግኝቷል።

በዚህ ዉድድር መከላከያ አትሌቲክስ ክለብ አጠቃላይ አሸናፊ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል።

እንዲሁም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ሲያጠናቅቅ ኦሮሚያ ክልል አትሌቲክስ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ጨርሷል።

በሻምፒዮናው መዝጊያ በአትሌቲክስ ስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ተጠባቂ የሆኑ 10 የፍፃሜ ውድድሮች ተካሂደዋል።

በዚህም 5 ሺህ ሜትር ሩጫ ወንዶች ፍፃሜ ውድድር አትሌት አሊ አብዱለመና ከደቡብ ፖሊስ ቀዳሚ ሆኖ አጠናቋል።

ጥላሁን ኃይሌ ከደቡብ ፖሊስ ሁለተኛ ሲሆን ጌትነት ዋለ ከሲዳማ ቡና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ጨርሰዋል።

በሴቶች 5 ሺህ ሜትር ሩጫ ውድድር ፍፃሜ አትሌት ፈንታዬ በላይነህ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አንደኛ፤ ብርቱኳን ወልዴ ከሲዳማ ቡና ሁለተኛ፤ አትሌት መልክናት ውዱ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሶስተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።

በሴቶች 1 ሺህ 500 ሜትር ውድድር ደግሞ አያል ዳኛቸው ከመከላከያ አንደኛ፣ ዳዊት ስዩም ከመከላከያ  ሁለተኛ፤ ውብርስት አስቻለው አማራ ክልል አትሌቲክስ ቡድን ሶስተኛ ሆነው ጨርሰዋል።

በወንዶች 1 ሺህ 500 ሜትር አትሌት አድሃና ካህሳይ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤ መልካሙ ዘገየ ከሲዳማ ቡና፤ በድሩ ሱሩር ከደቡብ ፖሊስ እንደየቅደም ተከተላቸው ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በዛሬው እለት በሁለቱም ፆታ የዱላ ቅብብልና የሜዳ ላይ አትሌቲክስ ተግባራትም ተደርገዋል።

በዚህ ሻምፒዮና ውድድር ውጤታማ የሆኑ አትሌቶች በያዝነው ዓመት በሞሪሺየስ በሚካሄደው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ እንደሚካፈሉ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም