ድርጅቱ የስምሪት ቁጥጥርና የትራንስፖርት ፍሰትን ማቀላጠፍ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ሊተገብር ነው

168

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 24/ 2014 (ኢዜአ) የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ የአገልግሎት ድርጅት የስምሪት ቁጥጥር እና የትራንስፖርት ፍሰቱን ማቀላጠፍ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ሊተገበር መሆኑን ገለጸ።

ድርጅቱ ከዓለም ባንክ ባገኘው የ30 ሚሊዮን ዶላር ብድር ቴክኖሎጂን የማዘመንና የ110 ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተገጠመላቸው አውቶብሶች ግዥ ለመፈጸም እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመዋል።

የድርጅቱ ዋና ስራስኪያጅ አቶ ገበየሁ ዋቄ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ድርጅቱ በተለይም የአገልግሎት አሰጣጡን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ እየሰራ ነው።

በዚህም ወደ ስራ ለማስገባት የታሰበው 'አይ.ቲ.ኤስ' የተባለ ቴክኖሎጂ የድርጅቱን አሰራር የሚያዘምን ይሆናል ብለዋል።

በተጨማሪም ቴክኖሎጂው ሲተገበር በዋናነት የስምሪት ቁጥጥሩን እና የትራንስፖርት ፍሰቱን ማቀላጠፍ የሚያስችል እንደሆነ ጠቁመዋል።

'አይ.ቲ.ኤስ' ቴክኖሎጂ የድርጅቱ ደንበኞች የኤሌክትርኒክ ቲኬት (ኢ-ቲኬት) መጠቀም እንዲችሉ የሚያደርግም ነው ብለዋል።

ቴክኖሎጂው ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል አውቶቡሶች ከዴፖ (መቆሚያ ስፍራ) የሚወጡበትን ሰዓት በቀላሉ ማወቅ ማስቻሉ አንዱ ነው።

በተጨማሪም የአውቶቡሶች የምልልስ መጠን፣ ምን ያህል ኪሎ ሜትር መሄድ እንደቻሉ፣ ምንያህል ህዝብ እንዳጓጓዙ በቀላሉ ማወቅ የሚያስችል ቴክኖሎጂ እንደሆነም ተናግረዋል።

እንደ ስራ አስኪያጁ ገለጻ፣ ቴክኖሎጂው ጠንካራ ነገሮችን የበለጠ ለማሻሻልና ጉድለቶችን ለማረምም ትልቅ ፋይዳ አለው።

በሌላ በኩል ድርጅቱ ከከተማ አስተዳደሩ ድጎማ ለመላቀቅና የገቢ አቅሙን ለማሳደግ የማስታወቂያ ስራዎችን ለማጠናከር ማሰቡንም ጠቅሰዋል።

በዚህም በአውቶቡሶቹ ውጫዊ አካል ላይ፣ የውስጥ ቴሌቪዥኖች ላይ ማስታወቂያዎችን በመለጠፍ ተጨማሪ ገቢ የሚገኝበትን መንገድ ለማጠናከር እየሰሩ መሆኑንም ጨምረዋል።

አንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት በአዲስ አበባ ከተማና ዙሪያዋ ከ630 በላይ የሚሆኑ አውቶብሶችን ተጠቅሞ በየቀኑ ከ6 መቶ ሺ ህዝብ እያጓጓዘ እንደሚገኝ ተገልጿል።

አንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት በ1935 ዓ.ም የተቋቋመ ድርጅት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም