ከተሞች በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አሰጣጣቸው የነዋሪዎችን እርካታ ማረጋገጥ እንዲችሉ እየተሰራ ነው

294

ጎንደር፤ መጋቢት 23/2014 (ኢዜአ) ከተሞች ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎትን ግልጽ፣ ቀልጣፋና ተደራሽ በማድረግ የነዋሪዎችን እርካታ ማረጋገጥ እንዲችሉ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በከተሞች የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አሰጣጥና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአገልግሎት ስርዓት ላይ ያተኮረ የልምድ ልውውጥና የአውደ ጥናት መድረክ በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ነው።

 የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የፌደራል ከተሞችና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ፋንታ ደጀን በመድረኩ እንደተናገሩት ከተሞች ለሀገር አቀፍ ልማት ፋይዳቸው የጎላ በመሆኑ አገልግሎት አሰጣጣቸውን ከኋላ ቀርና ልማዳዊ አሰራር ማላቀቅ ይገባል።

ዜጎች በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ቀልጣፋ፣ ውጤታማ፣ ግልጽና ተደራሽ አገልግሎት እያገኙ እንዳልሆነም በምዘና  ውጤታቸው ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል።

ይህን ለመለወጥ መንግስት በ10 ዓመት የልማት ዕቅዱ ከተሞች የምርታማና የብልጽግና ማዕከል እንዲሆኑ የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የከተሞችን አሰራር ለማዘመን የአሰራር ማዕቀፎችን ከማዘጋጀት ባለፈ ለከተማ አመራሮችና ፈጻሚዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን አስረድተዋል።

"መድረኩ ከተሞች ምርጥ ተሞክሮዎቻቸውን በመቀመር በከተሞች መካከል ልምድ የመለዋወጡ ሥራ እንዲጠናከር ለማገዝ ያለመ ነው" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ፕሬዚዳንት ረዳት ፕሮፌሰር ጸጋዬ ቱኬ ናቸው።

የትብብር መድረኩ የከተሞች ፍላጎት ላይ መሰረት በማድረግ አውደ ጥናት፣ ስልጠና እና የልምድ ለውውጥ እንደሚያመቻች አመልክተዋል።

ይህም ከተሞቹ ለነዋሪዎቻቸው ምቹ የመኖሪያ አካባቢንና ዘመናዊ የአገልግሎት አሰጣጥን እንዲዘረጉ ለማስቻል ፋይዳው የጎላ መሆኑን ነው ያስረዱት።

ረዳት ፕሮፌሰር ጸጋዬ እንዳሉት፤ የትብብር መድረኩ ከተመሰረተ 11 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም የ5 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ እየተዘጋጀ ነው።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተወካይ አቶ ሙሉጌታ ታደሰ በበኩላቸው፤ ከተማዋን ለኑሮና ለሥራ ምቹ ለማድረግ በርካታ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በከተማው በመንግስትና በዓለም ባንክ የተቀናጀ በጀት ከ530 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ 190 የልማት ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

"የልምድ ለውውጥ መድረኩ የከተማውን አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን ያግዛል " ብለዋል።

በመድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ የደረቅ ቆሻሻ፣ የቄራዎች እና የከተሞች ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር (ካዳስተር) አገልግሎት አሰጣጥ ተሞክሮ ቀርቧል።

የከሚሴ ከተማ የመሬት ልማት ማኔጅመንትና በቴክኖሎጂ የተደገፍ የአግልግሎት ስርዓት እንዲሁም የደብረ ብርሃን ከተማ የኢንቨስትመንት አገልግሎት አሰጣጥ ተሞክሮ በመደረኩ የሚቀርቡ ሲሆን  ውይይት እንደሚደረግባቸው ታውቋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረኩ ከሀገሪቱ ከ60 በላይ ከተሞችን ወክለው የመጡ የሥራ ሃላፊዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም