በአዲሱ ዓመት በፍቅርና በይቅርታ ለውጡን ማስቀጠል ይገባል- የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች

52
ወልድያ ነሀሴ 30/2010 በአዲሱ ዓመት በቀልን በማስወገድ የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ በፍቅርና በይቅርታ ማስቀጠል እንደሚገባ በወልድያ ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለፁ። የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መላከ ገነት ዓለሙ አስማረ በሰጡት አስተያየት በአዲስ ዓመት በአዲስ አስተሳሰብና በብሩህ ተስፋ ለስራ ታጥቆ መነሳት ይገባል፡፡ የወልድያና በአካባቢው ከተሞች በዚህ አመት በተከሰተው መብትን የማስጠበቅ ትግል የንጹሀን ሕይወት የጠፋበትና በርካታ ንብረት የወደመበት እንደነበር አስታውሰው "በመጭው አዲስ ዓመት ያለፈውን በይቅርታ ትተን የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ተረባርበን ማስቀጠል ይጠበቅብናል’’ ብለዋል፡፡ አዲሱ ትውልድ ለለውጥ መስዋእትነት እንደከፈለው ሁሉ  በአዲሱ አመት ከስሜታዊነት በመንጻት አርቆ አሳቢነትን በመላበስ ለውጡን እንዲያስቀጥል መክረዋል ። በወልድያ ከተማ የቀበሌ 04 ነዋሪና የሃገር ሽማግሌ ሃምሳ አለቃ መላኩ ተገኘ በበኩላቸው "ወጣቱ ለለውጥ መስዋእትነት እንደከፈለ ሁሉ በአዲሱ አመት የይቅርታ ባህልን በማጎልበት ጅምሩን ማስቀጠል አለበት" ብለዋል ። "በአዲሱ አመት ሁሉም ዜጋ የይቅርታ ባህልን በማጎልበት ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል መጣር ይጠበቅበታል" ሲሉም ተናግረዋል ። በወልድያ ዩኒቨርስቲ የለውጥና የመልካም አስተዳደር ዳይሬክተር መምህር ጸሐፈላሕም ገብረአምላክ በህዝብ ትግል የመጣውን ለውጥ ለማስቀጠል ሕዝብና መንግስት እጅና ጓንት መሆን እንዳለባቸው ገልጠዋል፡፡ በተለይ ወጣቱ በቀልን በመርሳት በፍቅርና ይቅርታ መንፈስ ለውጡን እንዲያስቀጥል መክረዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም