ኢቦላ በኢትዮጵያ እንዳይከሰት እየተሰራ ነው

3660

አዲስ አበባ  ግንቦት 10/2010 የኢቦላ በሽታ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ እንዳይከሰት ለመቆጣጠር የዝግጅት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

በዓለም የጤና ድርጅት መረጃ መሰረት የኢቦላ በሽታ በኮንጎ ቢኮሮ በሚባል አካባቢ መከሰቱን የአገሪቱ መንግስት አስታውቋል።

ባለፉት አምስት ሳምንታት በበሽታው ከተጠረጠሩ 25 ህሙማን መካከል የ17 ሰዎች ህይወት ማለፉም ተገልጿል።

የበሽታው ምልክት ከታየባቸው አምስት ሰዎች ውስጥ ሁለቱ የኢቦላ ቫይረስ እንደተገኘባቸው መረጋገጡም ተጠቅሷል።

ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማዕከል ከሚመለከታቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመሆን በሽታው በአገሪቱ እንዳይከሰት እየሰራ ይገኛል።

ወረርሽኙ ከተከሰተም በሰው ህይወት ላይ ከፍተኛ የሞት አደጋ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና ሳያደርስ ለመቆጣጠር በመሰራት ላይ መሆኑን በመግለጫው አመልክቷል።

የኢቦላ በሽታ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ባለድርሻ አካላት ለበሽታው ልዩ ትኩረት በመስጠት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅትና ድጋፍ እንዲያደርጉም ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።

ከኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማዕከል ጋር የተጠናከረ የመረጃ ልውውጥ እንዲኖራቸውም ጠይቋል።