በክልሉ በአዲስ መልክ ለተዋቀሩ ወረዳዎች መሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ

283

አሶሳ ፤ መጋቢት 22 /2014 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን በአዲስ መልክ ለተዋቀሩ ሁለት ወረዳዎች የመሠረት ልማት ግንባታዎች ለማስጀመር የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ፡፡

የክልሉ ምክር ቤት በተያዘው  ሳምንት  አሶሳ ወረዳ "አብረሃሞ"  እና "ኡራ"  በሚል ስያሜ በሁለት ወረዳዎች እንደገና እንዲዋቀር መወሰኑ ይታወሳል።

ውሳኔን  የማስፈጸም ስራ ተጀምሯል፡፡

ለዚህም በወረዳዎቹ የክልሉ እና የፌደራል ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ነዋሪው ህብረተሰብ  በተገኘበት ትናንት እና ዛሬ  የመሠረተ ድንጋይ ማስቀመጥ ሥነ-ሥርዓት ተካሄዷል።  

የአሶሳ ዞን  ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንድሪስ መሃመድ ለኢዜአ እንዳሉት ፤በሁለቱ የወረዳ ከተሞች በየዓመቱ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት መሠረተ ልማት ግንባታ ለመካሄድ ታቅዷል።

ከእቅዱም የወረዳ አስተዳድር ጽህፈት ቤቶችን ጨምሮ፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የመንገድ እና ሌሎችም ግንባታዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የአብረሃሞ ከተማ 50 ሄክታር ፤ የኡራ ከተማ ደግሞ 80 ሄክታር መሬት ስፋት ያለው ማስተር ፕላን እየተዘጋጅላቸው መሆኑን ጠቁመው በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ አሰታውቀዋል፡፡

በከተሞቹ ማስተር ፕላን ዝግጅት በተለይም ኢንቨስትመንት ማስፋፊያ የሚውሉ ቦታዎች ትኩረት እንደተሰጣቸው አቶ እንድሪስ አስረድተዋል፡፡

የህብረተሰቡን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ ከብሄርተኝት የጸዳ አመራር ያስፈልጋል ያሉት አቶ እንድሪስ ፤ በወረዳው የሚመደቡ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎችም መስፈርት ኢትዮጵያዊ አንድነትን መሠረት ያደረገ ይሆናል ብለዋል፡፡

ከሃገራዊ ለውጡ በኋላ በክልሉ እውነተኛ ፌደራሊዝም እየተተገበረ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ በህዝቡ ፍላጎት የተዋቀሩትን እነኚሁ ወረዳዎችን በአብነት ጠቅሰዋል፡፡

ከኡራ ወረዳ ነዋሪዎች መካከል የሃገር ሽማግሌ የሆኑት አብዲን ኢትማን በሰጡት አስተያየት በወረዳ የመደራጀት ጥያቄያቸው ከ30 ዓመት በላይ ያስቆጠረ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የረጅም ጊዜ ጥያቄአቸው በመመለሱ ደስተኞች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የአካባቢው ወጣቶች ተደራጅተው በመሰረተ ልማት እና ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ የስራ እድል እንደሚፈጠርላቸው ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ሁለቱ ወረዳዎች እያንዳንዳቸው በ41 ቀበሌዎች መደራጀታቸውንና በአጠቃላይ 300 ሺህ የሚገመት ህዝብ እንደሚኖርባቸው ከዞኑ አስተዳድር የተገኘ መረጃ ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም