መንግስት ለግብርናው ልማት የሰጠውን ትኩረት ማጠናከሩ የውጭ ተፅዕኖን ለመቋቋም ያግዛል

128

ሀዋሳ፤ መጋቢት 22/2014 (ኢዜአ) መንግስት ለግብርና ልማት የሰጠውን ትኩረት አጠናክሮ ማስቀጠል ሀገሪቱን ለመጉዳት የታሰበው የውጭ ተፅዕኖ ለመቋቋም እንደሚያግዝ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ምሁራን ተናገሩ።

" ኤች አር 6600"  ረቂቅ ህግ ቢጸድቅ እንኳን የውስጥ አቅምን በመጠቀም ጉዳቱን ለመቋቋም የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባ ተመልክቷል።

ረቂቅ ህጉ ያዘጋጁት  የሕወሓት ደጋፊዎች ለአሜሪካ የተወሰኑ የኮንግረስ አባላትና ሴናተሮች በከፈሉት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መሆኑን መረጃዎች ያስረዳሉ።

ዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስና አለም አቀፍ ጥናት መምህር አቶ አወል አሊ፤ አሜሪካኖች የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት ሲሉ ጥቅማቸውን ለማስከበር የማይፈልጓቸውን ሀገራት ሲያፈርሱ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።

በሀገራት የውስጥ ጉዳያቸው ጣልቃ በመግባት አልሳካ ካላቸው አሳሪ ህጎችን በማውጣት አልያም በቀጥታ በመውረር ተገቢ ያልሆነ ተግባር ሲፈጽሙ እንደነበር  አፍጋኒስታንን በማሳያነት አንሰተዋል።

በሀገራችንም አሸባሪውን የህወሃት  ቡድኑን በመደገፍ የተለያዩ ተፅዕኖዎችን ሲያደርጉ የነበረው አልሳካ ሲላቸው የተወሰኑ የኮንግረስ አባላትና ሴናተሮች "ኤች አር 6600" እና "ኤስ 3199 "  ህጎችን አርቅቀው ለማሽመድመድ እየተራወጡ ናቸው ብለዋል።

ይህ ህግ ቢጸድቅ በሀገራችን ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ቢሆንም ይህን ለመቋቋም መንግስት የተለያዩ አማራጮችን መጠቀም እንዳለበት ጠቁመዋል።

በዋናነት የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ መንግስት የሰጠውን ትኩረት አጠናክሮ በማስቀጠል ሊደረስ የሚችለውን ተፅዕኖ ለመቋቋም እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

በዚህም ራስን ለመቻል መስራትና በኢኮኖሚው የጠነከሩ አዲስ አጋር ሀገራትን በአማራጭነት ማየት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

ከዚህ ባለፈ የውስጥ አንድነታችንና ኢኮኖሚ አቅማችንን በማጠናከር ሀገራችን ማንም በፈለገ ሰዓት ህግ እያወጣ የሚያሽመደምዳት እንዳትሆን መስራት እንደሚገባም አመልላክተዋል።

ማንኛውም አማራጮች በመጠቀም ራሳችንን ለመቻል በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት ምሁሩ።

እንዲሁም በሀገር ውስጥ ሰላምን ማረጋገጥ፣ የተጀመሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለኢኮኖሚው አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበትን እድል መፍጠርና የጎላ አስተዋጽኦ የሌላቸውን ፕሮጀክቶች በማቋረጥ ሀገር ከተረጋጋ በኋላ ማስቀጠል እንደ አማራጭ ሊታዩ ይገባል ሲሉም ጠቁመዋል።

በዩኒቨርሲቲው የአለም አቀፍ ግንኙነትና አልሙኒ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዮሀና ዮካሞ በበኩላቸው፤ የተወሰኑ የአሜሪካ ኮንግረስ አባላትና ሴናተሮች በአሸባሪው ህወሃት ደጋፊዎች ተከፍሏቸው በኢትዮጵያ ላይ ለመተግበር ያዘጋጁት " ኤች አር 6600 " እና "ኤስ 3199 "ረቂቅ ህጎች ጸድቀው ወደ ትግበራ ቢያመሩ አብረውን የሚቆሙ አጋር ሀገራትን ከአሁኑ ማሰብ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ራሳችንን እንደ ደሴት አጥረን መቀመጥ ሳይሆን ከራሷ ከአሜሪካንም ሆነ ከሌሎች ሀገራት ጋር በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ መስራት እንደሚገባም እንዲሁ።

የትኛውም ህግ የሀገራችንን ሉአላዊነት  የሚነካ መሆን እንደሌለበት ያመለከቱት ምሁሩ፤  በሉአላዊነት ጉዳይ ወደኋላ መሄድ አይገባም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ያላት አቀማመጥ በአፍሪካ ቀንድም ሆነ በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ሀገራትን ለመቆጣጠር ስትራተጂክ ሀገር በመሆኗ ተጽዕኖው ከፍ እንዲል ያደረገው መሆኑን በማሰብ ይህንን ፈተና ለማለፍ አንድነትን በማጠናከር በጋራ መስራት ያስፈልጋል። 

ረቂቅ ህጎቹ ቢጸድቁ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመቋቋም እንዲያግዝ መንግስት በተለይ ለግብርናው ልማት የሰጠውን ትኩረት አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት ምሁራኑ ተናግረዋል።

በአፍሪካ የጥናት ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪና በላይደን ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ፖለቲካ እና አስተዳደር ፕሮፌሰር  ጆን አቢንክ በአሜሪካ ኮንሰርቫቲቭ ድረ-ገጽ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ "ኤች.አር 6600"  ረቂቅ ህግ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች የፈጸማቸውን የጦር ወንጀሎች የማይገልጽና የአንድ ወገን አድሎአዊነት የሚንጸባረቅበት እንደሆነ ገልጸዋል።

ረቂቅ ሕጉ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ አድሎአዊ እና አቻ የለሽ ጣልቃገብነት የሚፈቅድ በመሆኑ ተገቢነት የለውም ብለዋል።

የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ የቆየ ወዳጅነትና የጋራ ጥቅምን አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን የባይደን አስተዳደር ሊገነዘበው እንደሚገባ ነው  ፕሮፌሰሩ ያብራሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም