በአሶሳ ዞን 10 ሺህ ሄክታር ጥብቅ ደን የመስክ ጂን ባንክ ሆኖ የካርታ ርክክብ ተካሄደ

384

አሶሳ ፤ መጋቢት 22 / 2014 (ኢዜአ ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን ሆሞሻ ወረዳ 10ሺህ ሄክታር ጥብቅ ደን የመስክ ጂን ባንክ ሆኖ የካርታ ርክክብ ተካሄደ፡፡

የካርታ ርክክቡ የተካሄደው  በክልሉ ክልል ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ እና  በሆሞሻ ወረዳ አስተዳደር  መካከል ነው።  

የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ በቀለ አንበሳ በካርታ ርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የፈረመችውን ዓለም አቀፍ የብዝሃ ህይወት ስምምነት በክልሉ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

ክልሉ ጥብቅ የተፈጥሮ ደን እና በርካታ የዱር እንስሳትን ጨምሮ ሰፊ ብዝሃ ህይወት የሚገኙበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ተፈጥሮ ሃብት ላይ በተለይ በህገወጥ እርሻ ምክንያት በሚደረግ የደን  ምንጣሮ በዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የአርሶ አደሩን ግንዛቤና  ከዘርፉ የሚያገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ምክትል ሃላፊው አስታወቀዋል፡፡

"የመስክ ጂን ባንክ" ሆኖ ዛሬ የካርታ ርክክብ መፈጸሙ  በመመናመንና የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸውን ብዝሃ ህይወት  በመታደግ እና አልምቶ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብቱን በጥናትና  ምርምር ስራዎች በማበልጸግ ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን ጠቀሜታ ለማሳደግ  እንደሚረዳም  ገልጸዋል፡፡

የሆሞሻ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሃሚድ ሳለ በበኩላቸው ፤የተፈጥሮ ሃብቶች ተጠብቀው ለትውልድ ካልተላለፉ ከጠፉ በኋላ መልሶ መተካት አዳጋች  መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወረዳው ለመስክ ጂን ባንክ ያስረከበው 10 ሺህ ሄክታር መሬት የአካባቢው ማህበረሰብ ጠብቆ ያቆየው ጥብቅ የተፈጥሮ ደን መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

አስተዳደሩ በቀጣይም በአካባቢው ለሚካሄዱ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና የምርምር ስራዎች ስኬት ተግቶ እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡

በርክክቡ ሥነ-ሥርዓት ላይ ከተገኙት የወረዳው ነዋሪዎች መካከል አቶ አደም ሃሊል፤  በአካባቢው የሚገኘው ጥብቅ የተፈጥሮ ደን የጂን ባንክ ስራ ተግባራዊ በመደረጉ ደስተኞች ነን ብለዋል፡፡

ሃብቱ የበለጠ ተጠብቆ እንዲቆይ ከማድረጉ ባሻገር የስራ እድል ይፈጥርልናል ብለው እንደሚጠብቁም ገልጸዋል።

በቀጣይ የተፈጥሮ ደኑን በመንከባከብ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አቶ አደም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም