ባለፉት ዘጠኝ ወራት የጥራት ደረጃ ያላሟሉ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ተደርጓል

148

መጋቢት 22/2014(ኢዜአ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት የጥራት ደረጃ ያላሟሉ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ መደረጉን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ የንግድ ምርቶችን ጥራት በሚመለከት ከአምራቾች፣ ከጅምላ ነጋዴዎች፣ ከቸርቻሪዎች እና  ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡

በሚኒስቴሩ የገበያና ፋብሪካ ምርቶች ጥራት ቁጥጥር ዳይሬክተር ተከተል ጌቶ እንዳሉት፤ የገቢ ምርቶች ጥራታቸው እየተረጋገጠ እንዲገቡ ከማድረግ አንጻር ባለፉት ዘጠኝ ወራት ጥሩ ውጤት ተመዝግቧል፡፡

በተጠቀሰው ወራትም የጥራት ደረጃ ያላሟሉ 1 ነጥብ 815 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ከተደረጉ ምርቶች መካከል አምፖል፣ የኤሌክትሪክ መከፋፈያ፣ የኤሌክትሪክ ኬብል፣ የአርማታ ብረት፣ የአተር ክክ፣ ሩዝ፣ ቀይ ሽንኩርትና የስንዴ ምርት እንደሚገኙም አብራርተዋል፡፡

በተመሳሳይ የወጪ ምርቶች የተቀባይ አገራት መስፈርቶችን እያሟሉ እንዲወጡ ከማድረግ አኳያም አበረታች ተግባራት ተከናውኗል ብለዋል፡፡

በ450 ሺህ ሜትሪክ ቶን የወጪ ምርቶች ላይ ቁጥጥር ለማድረግ ታቅዶ በ360 ሺህ 739 ሜትሪክ ቶን ምርቶችን ላይ ቁጥጥር ማድረግ መቻሉንም አንስተዋል፡፡

በአገር ውስጥ የሚመረቱም ሆነ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች የተቀመጠውም የጥራት መስፈርት ማሟላት እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ በተለያዩ የገበያ እና የአምራች ኢንዱስትሪ ስፍራዎች በመዘዋወርና ወካይ ናሙና በመውስድ የምርቶችን ጥራት ደረጃ በላብራቶሪ የማረጋገጥ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

በዚህም የጥራት ደረጃ ባላሟሉ  አምራች ድርጅቶች ላይ ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ጀምሮ  ንግድ ፈቃድ እስከመንጠቅ የሚደርስ እርምጃ የተወሰደ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

አምራችና አከፋፋይ ድርጅቶች ስራቸውን በኃላፊነት እንዲሰሩም ነው ያሳሰቡት፡፡

በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ የደረጃ ዝግጅት ዳይሬክተር አቶ ይልማ መንግስቱ በበኩላቸው፤ የምርት ጥራት ደረጃ ማውጣት በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም አምራች ኢንዱስትሪዎች ይህንን ታሳቢ በማድረግ ስራቸውን እንዲያከናውኑ ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም