በመናኸሪያዎች እየተስተዋለ ያለው ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ ተገልጋዩን ለእንግልት ዳርጓል

120

መጋቢት 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) በመናኸሪያዎች እየተስተዋለ ያለው ሕገ-ወጥ የደላሎች እንቅስቃሴና የታሪፍ ጭማሪ ለተጨማሪ ወጪና ለእንግልት እንደዳረጋቸው ተገልጋዮች ገለፁ።

የኢዜአ ሪፖርተር በቃሊቲና ላምበረት መናኸሪያዎች የትራንስፖርት አገልግሎትን ቅኝት አድርጓል።

በምልከታው የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት በርካታ ሰዎች በብርድና በጸሃይ ረጃጅም ሰልፎችን ሲጠብቁ ተመልክቷል።

አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት ሕገ-ወጥ ደላሎች ከአሽከርካሪዎች ጋር በመመሳጠር ከመናኸሪያ ውጭ በመጫን የትራንስፖርት እጥረት እየፈጠሩ ነው።

መንግሥት ካወጣው ታሪፍ በላይ ደላሎች በሚወስኑት ታሪፍ እንድንከፍል እየተገደድንም ነው ብለዋል።

ከታሪፍ በላይ ከመክፈል ባሻገር በመናኸሪያዎቹ ሕገ-ወጥነትና ዝርፊያም በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍቶ ቀጥሏል ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ።

ይህንንም ተከትሎ የሚመለከተው አካል ጉዳዩ በአንክሮ ተመልክቶ አፋጣኝ መፍትሄ ይስጠን ሲሉ ጠይቀዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል አቶ ኪዳኔ ብርሃኑ መንግስት ይህንን ችግር በአፋጣኝ አይቶ መፍትሄ እንደሰጠን እንጠይቃለን ሲሉ ገልጸዋል።

ሌላኛው  አስተያየት ሰጪ ኃይሉ በቀለ በበኩላቸው ይህን ችግር እየፈጠሩት ያሉት ደላሎች መሆናቸውን ገልጸ፤ በዘርፎ የተሰማሩት አካላት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ችግሩን ሊቀርፈው ይገባል ሲል ተናግሯል።

ተሳፋሪዎቹ በተለይ ቅዳሜና እሁድ በመናኸሪያዎቹ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት ረጅም ሰልፍ እንዳለ ገልፀው አብዛኛው ተሽከርካሪ በህገ-ወጥ መንገድ ከመናኸሪያ ውጭ ስለሚጭኑ ነው ብለዋል።

ኅብረተሰቡ ለረጃጅም ሰልፎች የተዳረገው መንግሥት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ ባለመሆኑ ነው ያሉት ደግሞ የቤተከኒሳ ማኅበር የቃሊቲ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅና የማኅበራት ተወካይ ድሉ በየነ ናቸው።

ሰልፍ ሲበራከት አሽከርካሪዎችን ከመደበኛ መስመራቸው ሌላ ሥምሪት ተሰጥቷቸው የኅዝብ ክምችት ወረቀት ይዘው እንዲያገለግሉ ቢሆንም በመዳረሻ ቦታዎች አሽከርካሪዎች እየተከሰሱ በመሆኑ ይህንን ችግር ለመፍታት ከክልሎች ጋር በቅንጅት መሥራት ይገባልም ብለዋል።

ይሁንና የላምበረት መናኸሪያ የኅዝብ ትራንስፖርት ስምሪት ክትትል አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ጌታሁን ቸሩ  ከመናኸሪያው በቀን በአማካይ 400 መለስተኛ ተሽከርካሪዎች ምልልስ ሲያደርጉ 40ዎቹ ደግሞ አገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ተሽከርካሪዎች በየወሩ በሚፀድቅላቸው መርሃ ግብር መሰረት  በተቀመጠላቸው ታሪፍ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልፀው የታሪፍ ጭማሪ በሚያደርጉ ላይ ቁጥጥር በማድረግ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።

ኅዝብ በአንድ መነሻ ላይ ሲበዛ በልዩ ጉዞ ማስፈፀሚያ መመሪያ መሰረት ከመደበኛው እስከ 50 በመቶ ድረስ ጭማሪ ተደርጎ የሌላ መስመር ተሽከርካሪዎች እንዲጭኑ እንደሚደረግ ጠቅሰዋል።

ከዚህ ውጪ ታሪፍ የሚጨምሩ ላይ ከግቢ ሳይወጡ ጀምሮ ክትትል እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

የቃሊቲ መናኸሪያ አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ረታ ነጋሳ በበኩላቸው የተሽከርካሪ ምልልሶችን ቀልጣፋ ለማድረግ እየሰራን ነው ብለዋል።

ከመነኸሪያ ውጪ ከትራንስፖርት ታሪፍ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን አረጋግጠው እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ከጸጥታ ሃይሎች ጋር ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመዋል።   

ጎን ለጎንም ከታሪፍ በላይ ማስከፈልና ረጃጅም ሰልፎችን መሰለፍ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።     

የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ እየታየ ያለውን ችግር ለመፍታት እያከናወነ ያለውን ተግባር በተመለከተ መረጃ እንዲሰጥ ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም