አንዳንድ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከአሰራር ውጪ ተማሪዎችን ተቀብለዋል

161

መጋቢት 22/2014 (ኢዜአ)  አንዳንድ የግል ከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎች ከተፈቀደላቸው የተማሪዎች ቅበላ መጠን በላይ ተማሪዎችን መቀበላቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኦዲት ግኝት ጠቅሶ አመላከተ።

የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ2012/13 የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፈቃድ አሰጣጥና ጥራት ቁጥጥር የክዋኔ ኦዲት ግኝት ሪፖርት ላይ ውይይት አድርጓል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ ተቋሙ የነገ አገር ተረካቢ ትውልድ ለመቅረፅ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለመቅረፍ ከተሰጠው ሃላፊነት አንጻር ውስንነቶች ይታይበታል ብለዋል።

ቋሚ ኮሚቴው በኦዲት ግኝቱ በአዲስ አበባ በሚገኙ 17 የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ላይ  በወሰደው ናሙና የእውቅና ስታንዳርድና የብቃት ማዕቀፍ መመሪያ ማግኘት አለመቻሉን አሳይቷል።

በናሙናው ተቋማቱ መመሪያዎችን በመጣስ በመጀመሪያ ዲግሪና በማስተርስ ድግሪ ከ180-200 በመቶ  ተማሪዎች ተቀብለው የሚያስተምሩ መሆናቸውን ኦዲት ግኝቱ እንደሚያሳይ አመላክቷል።

ቋሚ ኮሚቴው የብቃት ምዘና ማረጋገጫ ሲኦሲ ሳይወስዱ በዲግሪ መርኃ ግብር የሚማሩ ተማሪዎች መኖራቸውን ማረጋገጡን የኦዲት ሪፖርቱን ጠቅሰው ተናግረዋል።

እንዲሁም በተቋማት ውስጥ ከሚያስተምሩ መምህራን መካከል ፔዳጎጂ ያልወሰዱ እንዳሉ በኦዲት ግኝቱ ወቅት መታየቱን አንስተዋል።።

ባለሥልጣኑ ከጤናና ከህግ ተማሪዎች በስተቀር በሌሎች የትምህርት መስኮች የሙያ ብቃት ምዘና የሚካሄድበት የአሰራር ሥርዓት አለመዘርጋቱና ለተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና የማይሰጥ መሆኑን የክዋኔ አዲት ግኝቱ አመላክቷል።

ምዘናውንም ተግባራዊ በማያደርጉ ተቋማት ላይ ህጋዊ እርምጃ የመውሰድ ሥራ አለመስራቱ የኦዲት ግኝቱ ማሳየቱን ቋሚ ኮሚቴው አክሏል።

በአጠቃላይ ቋሚ ኮሚቴው በኦዲት ግኝት ላይ የተገኙ ክፍተቶች ለማሻሻል ተቋሙ የወሰዳቸው የእርምት እርምጃዎች አለመኖራቸውን አስታውቋል።

በዚህም የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን እስከ ሚያዚያ 8 ቀን 2014 ዓም ድረስ የኦዲት ግኝት ማስተካከያ የድርጊት መርሀ ግብር አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

በተጨማሪም ቋሚ ኮሚቴው በዘርፉ ላይ የታየውን ብልሹ አሰራር ለመፍታት አስፈላጊውን ምርመራ እንዲያደርጉ ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።

በዚህም በቀጣይ ሁለት ወራት የተቋሙን ችግሮች በመመርመር የመፍትሄ አቅጣጫዎችን የሚያዘጋጅ አምስት አባላት ያሉት ልዩ ኮሚቴ በመሰየም ያገኘውን ውጤት ለምክር ቤቱ እንዲያቀርብ አቅጣጫ ተቀምጧል።

የፌደራል ሥነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በባለስልጣኑ የተገኙ የኦዲት ግኝቶችን መነሻ በማድረግ ለሙስናና ብልሹ አሰራሮችን እንዲሁም አጋላጭ የሆኑ አሰራሮችን በመፈተሽ የታዩ ነገሮችን  በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ጊዜ እንዲያቀርብ አሳስቧል።

ቋሚ ኮሚቴው የፍትህ ሚኒስቴር በባለስልጣኑ የሥራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ከኦዲት ግኝቱ አንጻር የተገኙ በወንጀል የሚያስጠይቁ ጉዳዮች የሚኖሩ ከሆነ መርምሮ ክስ እንዲመሰርት አሳስቧል።

አያይዘውም ሕገ-ወጥ አካሄድ በሚከተሉ የትምህርት ተቋማት ባለድርሻዎች ላይ ተገቢ የሆነ የወንጀል ምርመራ በማድረግ ተጠያቂ በሚሆኑት ላይ ክስ እንዲመሰርት አሳስቧል።

አጠቃላይ የአፈጻጸም ሪፖርቱን በሁለት ወራት ውስጥ ለኮሚቴው እንዲያሳውቅ አቅጣጫ አስቀምጧል።

የፌዴራል ትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንዷለም አድማሴ በበኩላቸው በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መኖራቸውን አንስተው ይህንንም ለመፍታት ተቋሙ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ተቋሙ በሚሰራው ሥራ ላይ የአደረጃጀትና የሰው ሃይል ችግር ለሥራቸው ማነቆ እንደሆነባቸው አንስተዋል።

በቀጣይ በኦዲት ግኝቱ ወቅት በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፈቃድ አሰጣጥ፣ ቁጥጥርና በሌሎች ጉዳዮች ላይ የተገኙ ክፍተቶችን እንደ ግብዓት በመውሰድ ለማሻሻል እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

በመጨረሻም ቋሚ ኮሚቴው የትምህርት ሚኒስቴር በባለስልጣኑ የኦዲት ግኝት ላይ የተስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት እንዲሰራ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም