ታላቁን የረመዳን ወር በጎ ተግባር በመፈጸም ማሳለፍ ይገባል

113

መጋቢት 22/2014/ኢዜአ/ ታላቁን የረመዳን ወር በጎ ተግባር በመፈጸም ማሳለፍ ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር ኢድሪስ ተናገሩ።

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር ኢድሪስ የታላቁ ረመዳንን ወር ፆም አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚህም ረመዳን ሙስሊሞች ራሳቸውን ከምግብና ከመጠጥ ብቻ የሚያርቁበት ወር ሳይሆን፤ ከአላህ ጋር የሚቀራርቡበትና የግል ስሜታቸውንና ራስ ወዳድነታቸውን የሚያርቁበት ነው ብለዋል።

ታላቁ የረመዳን ወር የመረዳዳት፣ የመተጋገዝና የመከባበሪያ ወር በመሆኑ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ፈጣሪ የሚወደውን በጎ ተግባራትን በማከናወን ጾሙን ማሳለፍ ይገባዋል ነው ያሉት።

በመግለጫው "ወገን ለወገን በረመዳን፤ ማፍጠሪያ ለተቸገሩ፣ በጦርነት ለተፈናቀሉ ወገኖች የረመዳን አስቤዛ ሰደቃ ለሰላሳ ቀናት" የተሰኘ የበጎ አድራጎትና የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ይፋ ተደርጓል።

በዚህም ሙስሊሙ ማኅበረሰብ የጾሙን ወቅት ለተቸገሩ፤ በድርቅና በጦርነት ለተፈናቀሉ ዜጎችና ከሳዑዲ ተመላሽ ወገኖች የሰደቃ ድጋፍ በማድረግ በመርሃ ግብሩ እንዲሳተፉ ጠይቀዋል።

መርሃ ግብሩም በአፍሪካ ኅብረት አጠገብ ለመስጂድ ግንባታ በተከለለው ሥፍራ የተዘጋጀ ሲሆን በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።

1443ኛው የረመዳን ፆም፤ ጨረቃ ከታየች ቅዳሜ ካልታየች ደግሞ እሁድ እንደሚጀመር ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር በመግለጫቸው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም