በሐረሪ ክልል አርሶ አደሩ የከርሰ ምድር ውሃን ለልማት የመጠቀሙን ልምድ ማስፋፋት ይገባል-ኢንጂነር አይሻ መሐመድ

81

ሐረር ፤ መጋቢት 21/2014 (ኢዜአ) በሐረሪ ክልል አርሶ አደሩ የመንግስትን ድጋፍ ሳይጠብቅ በራሱ የከርሰ ምድር ውሃን አውጥቶ ለልማት እየተጠቀመበት ያለው ልምድ ማስፋፋት እንደሚገባ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ተናገሩ።

ሚኒስትሯ በሐረሪ ክልል  ኤረር ዶዶታ ወረዳ በመስኖ እየለማ የሚገኘውን የአትክልት ማሳ በተመለከቱበት ወቅት፤  የአካባቢው አርሶ አደር ምርጥ ዘር ፣ ፓምፖችና ቲክኖሎጂዎች ቢቀርቡለት የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆን መረዳታቸውን ገልጸዋል።

ይህም ሆኖ የአካባቢው አርሶ አደር  የመንግስትን ድጋፍ ሳይጠብቅ በራሱ የከርሰ ምድር ውሃን አውጥቶ እየተጠቀመበት ያለው ልምድ ማስፋፋት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ይህን መልካም ተሞክሮ ለሌላውም የኢትዮጵያ አርሶ አደር  ትምህርት እንደሚሆን ነው ሚኒስትሯ ያመለከቱት።   

ለማህበረሰቡ በቀጥታ  ፍጆታ የሚውሉ ምርቶችን በብዛት ማምረት ከተቻለ የክልሉን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባሻገር የኑሮ ውድነቱን ያረጋጋዋል ብለዋል።

የዝናብ ውሃን አቁሮ ለመጠቀም በክልሉ ግድብ እንደሚሰራ ጠቁመው፤ የሚገነባው ግድብ የከርሰ ምድር ውሃው እንዳይቀንስና የክልሉን የውሃ አቅርቦት ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ  እንደሚኖረው አስረድተዋል።

በክልሉ ያለው የእርሻ መሬት በስፋት ቢለማ ሐረሪን መመገብ እንደሚችል ያመለከቱት ሚኒስትሯ፤ የክልሉ መንግስት ዘርፉን ሊደግፈው እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ሌላው በምስክ ምልከታው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ በበኩላቸው፤ እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር   በግብርናው ዘርፍ ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በተለይም በሀገራቸው  መንግስት የሚደገፈው "ፌር ፕላኔት " ፕሮግራም   የድሬዳዋ አርሶ አደሮችን በምርጥ ዘር አቅርቦት ተጠቃሚ ማድረጉን አውስተው፤ ይህንን እድል ወደ ሐረሪ ክልል በማምጣት ለመጥቀም እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የግብርና ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ሚስራ አብደላ፤ የመስክ ምልከታው ዓላማ  በክልሉ በመስኖ የሚለሙ ማሳዎችና  ሊገነባ ለታሰበው ግድብ የሚሆን ቦታን ለመመልከት ነው።

አርሶ አደሩ በዝናብ ጠባቂነት ሳይወሰን ባሉ የውሃ አማራጮች በዓመት በመስኖ እስከ ሶስት ጊዜ እንዲያመርት በመደገፍ ከጎኑ እንደሚቆሙ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም