ከሳዑዲ አረቢያ ስደት ተመላሾችን ከአቀባበል እስከ መልሶ ማቋቋም ያለውን ሂደት ለማሳለጥ በቂ ዝግጅት ተደርጓል

109

መጋቢት 21 ቀን 2014/ኢዜአ/ ከሳዑዲ አረቢያ ስደት ተመላሾችን ከአቀባበል ጀምሮ አስከ መልሶ ማቋቋም ያለውን ሂደት ለማሳለጥ በቂ ዝግጅት አድርጎ ወደስራ መግባቱን የስደተኞች አቀባበል ብሔራዊ ኮሚቴ አስታወቀ።

ሳዑዲ አረቢያ ሪያድ ከተማ በተለያዩ እስር ቤቶች በችግር ውስጥ የነበሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን የመመለስና መልሶ የማቋቋም ሂደቱን ለማሳለጥ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተለያዩ ባለድርሻ ተቋማት የተካተቱበት ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱ ይታወሳል።

በዛሬው እለትም ከሳዑዲ አረቢያ ሪያድ ከተማ የነበሩ ስደተኞች አዲስ አበባ  ገብተዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብርቱካን አያኖ እና ሌሎች የስደተኞች ጉዳይ ብሔራዊ ኮሚቴ አባል ተቋማት አመራሮች ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በዚሁ ወቅት የተለያዩ የዲፕሎማሲ ተግባራትን በማከናወን ዜጎችን ወደ አገር መመለስ እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

በዚህም በ11 ወራት ውስጥ ከ102 ሺህ በላይ ዜጎች ወደአገር ቤት ለመመለስ ዕቅድ የተያዘ ሲሆን በዛሬው ዕለት በመጀመሪያ ዙር በረራ ወደ 500 የሚጠጉ ኢትዮጵያዊያን አዲስ አበባ ገብተዋል ነው ያሉት፡፡

እስካሁን ከ40 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ መመዝገባቸውን ገልጸው፤ እናቶችና ህጻናትን  ጨምሮ ልዩ ድጋፍ ለሚሹ ስደተኞች ቅድሚያ ተሰጥቷል ብለዋል።

ስደተኞችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ከክልሎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በአዲስ አበባም ጊዜያዊ ማረፊያ መዘጋጀቱን አብራርተዋል፡፡

በቀጣይ ቀናት በአንድ ቀን ልዩነት በቀን ሶስት በረራዎችን በማድረግ ዜጎችን ወደ አገር ቤት የመመለስ ስራው እንደሚከናወን ገልጸዋል።

አስፈላጊውን ስልጠናና ተሃድሶ በመስጠት ተመላሾቹን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም እንደሚሰራም እንዲሁ፡፡

የኮሚቴው አባል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው ተመላሾቹን ለማቋቋም ዝግጅት መደረጉን ገልጸው፤ በተለይም ለአረጋዊያን፣ ሴቶችና ህጻናት ቅድሚያ ይሰጣል ብለዋል።

በዛሬው እለት ወደ አገር ቤት ከተመለሱ ዜጎች መካከል 157 ቱ ህጻናት 341 ሴቶች መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

የስደተኞችና ስደት ተመላሾች አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን በበኩላቸው ተመላሾቹ ለችግር እንዳይጋለጡ ከ16 ባለድርሻ ተቋማት ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።

በዚህም ተመላሾችን ከማህበረሰቡ ለመቀላቀልና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንደሚደረጉም ገልጸዋል።

በመዲናዋ ለስደት ተመላሾች በተዘጋጁ ጊዜያዊ ማረፊያዎች የምግብ፣ አልባሳት፣ መገልገያ ቁሳቁስ መዘጋጀቱን የገለጹት ደግሞ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክትል ኮሚሽነር አቶ ነሲቡ ያሲን ናቸው።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሰሃርላ አብዱላሂ ፤ ጤና ሚኒስቴር ከስደት ለተመለሱ ዜጎች የህክምና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮና ሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት ዝግጅት አድርጓል ብለዋል።

ስደተኞች በብዛት የጤና እክል ስለሚያጋጥማቸው ከሆስፒታሎች ባሻገር ተኝተው ለሚታከሙ በተጠባባቂነት "ቦሌ ጨፋ" በሚባል ስፍራ የህክምና ማዕከል መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በለጋሽ ድርጅቶች በተገኘ ድጋፍ በግል ሆስፒታሎች እንዲገለገሉ ቅድመ ዝግጀት መደረጉንም እንዲሁ፡፡

በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሁለት አንቡላንሶችና ባለሙያዎችን በመመደብ በመንገድ ላይ የጤና ችግር ለሚያጋጥማቸው ዜጎች አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉንም አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም