በእስር ቤቶች ውስጥ ከነበርንበት አስከፊ ሁኔታ ወጥተን ለአገራችን በመብቃታችን ተደስተናል

79

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች ከነበርንበት አስከፊ ሁኔታ ወጥተን ለአገራችን በመብቃታችን ተደስተናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ከስደት ተመላሽ ዜጎች ገለጹ፡፡

መንግስት በእስር ቤት ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ኢትዮጵያዊያንን ወደ አገር ቤት ለመመለስ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡

በሳዑዲ አረቢያ ከ750 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን እንደሚኖሩ የሚገመት ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ ከ450 ሺህ በላይ የሚሆኑት በህገ-ወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ የገቡ መሆኑ ይነገራል፡፡

በዚህም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን በሳዑዲ አረቢያ ለእስር እንደተዳረጉ ይገለጻል፡፡

መንግስት በእስር ቤት የሚገኙ ዜጎችን ለመመለስ የተለያዩ የዲፕሎማሲ ጥረቶችን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን፤ በዛሬው እለትም ዜጎችን ወደ አገር ቤት የመመለሱን ስራ በይፋ ጀምሯል፡፡

ዛሬ ረፋዱ ላይ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አማካኝነት በሪያድ ከተማ ከሚገኙ ከእስር ቤቶች ወጥተው አዲስ አበባ የደረሱ ዜጎች የደስታ ስሜታቸውን በተለያየ መልኩ ገልጸዋል፤ የአገራቸውን መሬት ሲስሙም ተስተውለዋል፡፡

ላለፉት ስድስት ወራት በእስር ቤት የቆየችው ሮዛ አሊ እና ከ10 ዓመታት በፊት ወደ ሳዑዲ አቅንታ ለእስር ተዳረጋ የቆየቸው አገሬ አለባቸው ከበርካታ የችግር ጊዜያት በኋላ ወደ እናት አገራቸው በመመለሳቸው እጅግ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

መንግስት ሌሎች በእስር ቤቱ የሚንገላቱ ወገኖችን በተቻለው አቅም እንዲመልሳቸውም ጥሪ አቅርበዋል።

በተመሳሳይ ፍሬ ሕይወት ዓለማየሁ እና ጌጤ አሰበም በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ አረቢያ በመሄዳቸው ለከፋ ስቃይ መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

"ህገ-ወጥ ስደት በእኛ ይብቃ" ሲሉም ለሌሎች ኢትዮጵያዊያን መልዕክት አስተላለፈዋል።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ገንበቶ በበኩላቸው  ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር ወደ አገር ቤት የሚመለሱ ዜጎችን ሁኔታ የማረጋገጥ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚሁ መሰረትም እናቶች፣ ህጻናትና አረጋዊያንን በማስቀደም የመመለስ ስራው መጀመሩን ተናግረዋል።

ስደተኞችን የመመለስ ስራ ውስበሰብ ሂደት እንዳለው ጠቅሰው፤  የሳዑዲ አረቢያና በኢትዮጵያ መንግስት መግባባት ተደርሶ በሳምንት 9 በረራዎችን በማድረግ ዜጎችን የመመለስ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም