ታላቁን የረመዳን ወር በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን በመርዳት ማሳለፍ ይገባል-የእስልምና እምነት ተከታዮች

95

መጋቢት 21/2014/ኢዜአ/ ታላቁን የረመዳን ወር በተለያዩ ምክንያቶች በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን በመርዳት ማሳለፍ ይገባል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የእስልምና እምነት ተከታዮች ገለጹ።

ታላቁ የረመዳን ወር በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቁን ስፍራ ይይዛል፡፡

በመላው ዓለም በሚገኙ ሙስሊሞች ዘንድ በጉጉት በሚጠበቀው ረመዳን ቀኑን በጾም ማሳለፍ ምሽት ላይ ደግሞ ከቤተሰብና ከዘመድ ጋር ተሰብስቦ በአንድነት ማፍጠር የተለመደ ነው።

የእምነቱ ተከታዮች ወሩን በፍቅርና በፍስሃ ለመቀበል በየፊናቸው እምነቱ የሚያዘውን ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው የእምነቱ ተከታዮች እንደሚሉት፤ ታላቁ የረመዳን ወር ያለው ለሌለው በማካፈል አብሮነት የሚታይበት ጊዜ ነው፡፡

በመሆኑም በተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው የሚገኙ ወገኖችን ይበልጥ በማሰብና ያለንን በማካፈል ለማሳለፍ ተዘጋጅተናል ይላሉ፡፡

ሃጂ መንሱር ኢሳ  እና አሊ መሐመድ፤ ረመዳን ሁሉም ልቡን በማጽዳት ከፈጣሪ ጋር የሚገናኝበት ወር በመሆኑ እርስ በእርስ በመረዳዳትና አብሮነትን በማጠናከር ጾሙን ለማሳለፍ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

የረመዳን ወር በጎ ተግባር የሚከወንበት በመሆኑ ዖሙን አቅመ ደካማ ከሆኑ ወንድምና እህቶቻችን ጋር በአንድነት ለማሳለፍ መዘጋጀታቸውንም ነው የገለጹት፡፡

የእምነቱ ተከታዮች ታላቁን የረመዳን ወር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና በመንከባከብ ሊያሳልፍ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በረመዳን ወር መልካም ነገር ማድረግና አዕምሮን ከመጥፎ ነገር ማጥራት የሚጠይቅ በመሆኑ  ለሰላምና ለይቅርታ መዘጋጀት ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ አቶ ረዲ አህመድ እና አልዬ ይመር ናቸው፡፡

ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም