በአማራ ክልል የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት የሰብል ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እየቀረበ ነው

181

ባህር ዳር መጋቢት 21/2014 (ኢዜአ) በክልሉ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ከ741 ሺህ ኩንታል በላይ የሰብል ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እየቀረበ መሆኑን የአማራ ክልል ሕብረት ሥራ ማስፋፊያ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ያለፉት ስምንት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የንቅናቄ መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

 በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍና ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ የሰብልና የሸቀጣሸቀጥ ምርቶችን ዋጋ እየናረው መምጣቱን  የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ወልደትንሳኤ መኮንን በመድረኩ ላይ ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ የዋጋ ንረትን ለመከላከል በበጀት ዓመቱ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የተለያዩ የሰብል ምርቶችን ከአርሶ አደሩ በመግዛት ገበያውን ለማረጋጋት አቅዶ እየሰራ መሆኑንም ተናገረዋል።

እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴም በ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ከ741 ሺህ ኩንታል በላይ የሰብል ምርት ግዥ መፈፀሙን አስረድተዋል።

ከተገዛው ውስጥ ከ343 ሺህ ኩንታል በላይ የሰብል ምርት ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ እንደተቻለም ገልጸዋል።

"የሰብል ምርቱ በማህበራትና ዩኒየኖች በኩል ለተጠቃሚዎች እየደረሰ ሲሆን እየቀረበ ካለው የሰብል ምርት መካከልም በቆሎ፣ ጤፍ እና ስንዴ ይገኙበታል" ብለዋል።

ከአርሶ አደሩ ለመግዛት በዕቅድ የተያዘውን ምርት በቀጣይ ሙሉ በሙሉ ማሟላት እንዲቻል በፋይናንስ በኩል ያለውን እጥረት ለማቃለል ኮሚሽኑ ከአጋር አካላት ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሃይለማርያም ከፍያለው በበኩላቸው የዋጋ ንረቱን በዘላቂነት ለመፍታት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ግብርናውን ለማዘመን የሕብረት ሥራ ማህበራት የእርሻ ትራክተሮች፣ የሰብል ማጨጃና መውቂያ ኮምባይነሮችን ገዝተው ለአርሶ አደሩ በተመጣጣኝ ዋጋ ሊያቀርቡ እንደሚገባም ተናግረዋል።

በምግብ እህል ራስን ለመቻል እየተደረገ ባለው ሁሉን አቀፍ ጥረት የእርሻ መካናይዜሽን ሥራ እንዲስፋፋና ምርታማነት እንዲጨምር ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የሕብረት ሥራ ማህበራት ባለፉት 3 ዓመታት ገበያን በማረጋጋት አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን ያስታወሱት ደግሞ የፌዴራል ሕብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አብዲ ሙመድ ናቸው።   

በአሁኑ ወቅት በዓለምና በሀገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ምርቶች ዋጋ መናር የኑሮ ውድነትን በማባባስ ህብረተሰቡን ለችግር እያጋለጠ መሆኑን ተናግረዋል።

እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት ከአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና ሲዳማ ክልሎች አቅም ያላቸው 47 ዩኒየኖችን በመለየት አምራቹን ከሸማቹ ጋር እንዲያገናኙና ገበያውን እንዲያረጋጉ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

"በተጨማሪ እያጋጠመ ያለውን የፋይናንስ እጥረት ለመቅረፍ ከተለያዩ ባንኮች ጋር በመወያየት ችግሩ እንዲፈታ ለማድረግ እየተሰራ ነው" ብለዋል።  

በመድረኩ ላይ ከፌዴራል፣ ከክልልና ከሁሉም ዞኖችና የከተማ አተዳደሮች የተውጣጡ የህብረት ሥራ ማህበራት የሥራ ሃላፊዎች፣ የዩኒየን ሥራ አስኪያጆችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም